በየዘርፉ ለተመዘገቡ ስኬታማ የልማት ተግባራት የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በየዘርፉ ለተመዘገቡ ስኬታማ የልማት ተግባራት የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው
ጅግጅጋ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-በየዘርፉ ለተመዘገቡ ስኬታማ የልማት ተግባራት የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ መሆኑን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ገለጹ።
ጳጉሜን 3 የጽናት ቀን በሶማሌ ክልል ደረጃ በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።
በበአሉ ላይ የተገኙት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ እንደገለጹት ፣የሀገርን ሰላም በማጽናት ልማትን ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት የጸጥታ አካላት ሚና ከፍተኛ ነው።
እንደ ክልሉም ሆነ እንደ ሀገር ለተመዘገቡ ስኬታማ የልማት ተግባራት የጸጥታ አካላት ድርሻ የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
ጠንካራ ጽኑ መሠረት ያለው ሀገር ለመገንባት የህብረተሰቡ እና የጸጥታ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል ።
በክልሉ የተጀመሩ የልማት ተግባራትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ጽናት ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ መሀመድናጂ መሐመድ ናቸው።
ጽናት ህዝቦች ችግሮችን የሚያልፉበትና ወደ አዲስ ዕድል የሚቀይሩበት ተግባር ነው ብለዋል።
የሶማሌ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ መሐመድ መሐሙድ በበኩላቸው፤ የጽናት ቀንን ስናከብር አባቶቻችን ያወረሱንን ሀገር በማጽናት ለትውልድ ለማስተላለፍ ቃላችንን በማደስ ሊሆን ይገባል ብለዋል።
በበአሉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።