ቀጥታ፡

የሀገርን ሰላምና ልማት ቀጣይነትን የማረጋገጥ ተልዕኳችንን በጽናት እንወጣለን 

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-የሚቃጡ የጠላት ሴራዎችን በቅንጅት በማክሸፍ የሀገር ሰላምና ልማት ቀጣይነትን የማረጋገጥ ተልዕኳቸውን በጽናት ለመወጣት መዘጋጀታቸውን የአገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች ገለጹ።

''በፅናት ችግርን እንሻገር፤ በአንድነት የተሻለች ሀገር እንገንባ'' በሚል መሪ ሀሳብ  የ''ፅናት ቀን'' በሲዳማ ክልል ደረጃ በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ መርሀ ግብሮች ተከብሯል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አመራሮች የሀገር ሰላምና ልማት ቀጣይነት እንዲረጋገጥ ከውጭም ከውስጥም የሚቃጡ የጠላት ሴራዎችን በቅንጅት የማክሸፍ ተልዕኳቸውን በጽናት ለመወጣት ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።

የሀገርን ዘላቂ ሰላም በማረጋገጥ የተያዙ የልማት ግቦችን ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የሠራዊት አባላት ሚናቸውን አጠናክረው እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በሀገር መከላከያ ሠራዊት የደቡብ ዕዝ ጠቅላይ መምሪያ የጠቅላላ አገልግሎት መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል የሽዋስ ደምሴ እንደተናገሩት፤  የሠራዊት አባላት ለሀገር ሉአላዊነት መከበር በጽናት የሚከፍሉት የሕይወት ዋጋ መተኪያ የሌለው ነው።


 

የሠራዊቱ አባላት የሀገር ዳር ድንበርና ሉአላዊነትን በማስጠበቅ ግዙፍ የልማት ግቦች እንዲሳኩ በጽናት ሲሰራ መቆየቱን አስታወሰዋል፡፡ 

በጽናት መቆም ለወታደር ብቻ የሚተው አይደለም ያሉት ኮሎኔል የሽዋስ፣ ሁሉም ለሀገር ሰላምና እድገት በጽናት በመቆም የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት አለበት ብለዋል።

በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ የደቡብ ፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ መምሪያ የሰው ሀብት ሥራ አመራር ምክትል መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ሲሳይ ገላን በበኩላቸው፣ የሀገር ሰላምና ልማትን በዘላቂነት አጠናክሮ ለማስቀጠል ሠራዊቱ ማንኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ  ነው ብለዋል ።


 

በፀረ ሰላም ሀይሎች የሀገርና የህዝብ ሰላም እንዳይታወክ ለመከላከል የፌደራል ፖሊስ አባላት ሁልጊዜ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ እንዲፋጠን በየጊዜው የሚቃጡ የጠላት ሴራዎችን በቅንጅት የማክሸፍ ተልዕኮን በጽናት እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ህዝቡ የልማት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር የፖሊስ አባላት ሰላምን በዘላቂነት የማስጠበቅ ተልዕኳቸው ላይ አተኩረው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጽናት ቀንን ስናከብር ውስብስብ ፈተናዎች አልፋ በብልጽግና ጉዞ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ ልማቷን አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለንን ጽናት በማረጋገጥ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የሲዳማ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳዊት ዳንጊሶ ናቸው።


 

ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት ነጻነቷ ተጠብቆ የቆየችውን ኢትዮጵያ ልማቷን በማፋጠን ለቀጣይ ትውልድ ያደገች ሀገር  ለማስረከብ ሰላሟን በጋራ ልናጸና ይገባል ብለዋል።

የተጀመሩ የልማትና የብልጽግና ግቦችን ከዳር ለማድረስ ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በተናበበ መልኩ በጽናት የሚያደርገውን አስተዋጽኦ  እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ የሲዳማ ክልል ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ኮሚሽነር ተስፋዬ ዴቢሶ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም