ቀጥታ፡

 በድሬዳዋ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ ናቸው

ድሬዳዋ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- በድሬዳዋ አስተዳደር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ  የልማት ተግባራት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ  መሆናቸውን የአስተዳደሩ ከንቲባ ከድር ጁሃር ገለጹ።

በድሬዳዋ አስተዳደር በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተገነቡ  ቤቶች ዛሬ ተመርቀው ለተቸገሩ  የህብረተሰብ ክፍሎች ተላልፈዋል።


 

 የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ቤቶቹን መርቀው ቁልፍ አስረክበዋል።

ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደገለፁት ፤ በክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በ14 የተለያዩ  ዘርፎች  የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት እያሳደጉ  ናቸው።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በተለይ የአረጋዊያንን ቤቶች በአዲስ የመገንባትና የመጠገን ተግባራት አበረታች ውጤቶች እያስገኙ መሆናቸውን አንስተዋል።

ዛሬ በአስተዳደሩ ሴክተር መስሪያ ቤቶችና በግል ተቋማት  ተገንብተው ለተቸገሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተላለፉት ቤቶችም የዚሁ ማሳያ  መሆናቸውን ገልጸዋል ።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የልማት ስራዎችን ከማገዝ ባለፈ የእርስ በእርስ መረዳዳትና መደጋገፍ ባህል እንዲጎለብት ማድረጉን ጠቁመዋል።

እነዚህን ሰው ተኮር ልማቶች በማጠናከር ማህበራዊ ችግርን በጋራ የመሻገር ጉዞ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል ።


 

የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽነር ካሊድ መሐመድ በበኩላቸው፤ በዘንድሮ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት 350 አዳዲስ ቤቶችን የመገንባት እና 150 ቤቶችን  የመጠገን ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።

በበጎ ፈቃድ ስራዎቹም ወጣቶችን ጨምሮ 300 ሺ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ  መሆናቸውን ጠቁመው በአገልግሎቱ ከ299 ሺ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ  አመልክተዋል።

ወጣቶቹ  በበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች በአረንጓዴ አሻራ ችግኞችን በመትከል፣ ደም በመለገስ፣ ማዕድ በማጋራት ፣በሰላም ግንባታና በትራፊክ አደጋ በመከላከል፣ አረጋዊያንን በመንከባከብና በትምህርት ስራዎች  እየተሳተፉ መሆናቸውን የገለጹት  ደግሞ በኮሚሽኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ በሐር አደም ናቸው።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ በትውልድ ውስጥ የመተባበር ባህል እንዲሰርፅ መሠረት መጣሉንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም