ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ብቁና ዘመናዊ የሰው ኃይል የማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ለሀገራቸውና ለዜጎች የላቀ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ብቁና ዘመናዊ የሰው ኃይል የማፍራት ሀገራዊ ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ መሆኑን ገለጸ፡፡  

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ንጉሥ ታደሰ (ዶ/ር) ተቋሙ ያካሄደውን አጠቃላይ ተቋማዊ ሪፎርም አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው፤ ዩኒቨርሲቲው ተቋማዊ አቅሙን ለማጎልበትና ለመንግሥት ተቋማት ግንባታ የሚኖረውን ሚና ለማሳደግ ያለመ ሰፊ የሪፎርም ሥራ ሲያካሂድ ቆይቷል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተበት ሰላሳ ዓመታት ወዲህ ሦስት መሠረታዊ ደረጃዎችን ማለፉን ጠቅሰው፤ የመጀመሪያው አመራሮችን በማብቃት ላይ ያተኮረ፣ ሁለተኛው ደግሞ በየደረጃው የሚገኙ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን የማብቃት ሥራ የተከናወነበት እንደነበር ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ሦስተኛው እና አሁን ላይ የሚገኝበት ደረጃ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችንና በሥራ ላይ ያሉ የሲቪል ሰርቪስ ሠራተኞችን አዋህዶ መቀበልና ማስተማር እንደሆነ አብራርተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ወደዚህ አዲስ አካሄድ የተሸጋገረው ነባሩን ሠራተኛ ማብቃት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ነባሩን የሚተኩ ወጣት መሪና ሲቪል ሰርቫንት ማዘጋጀት ወሳኝ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ለአስተማማኝ ሪፎርም የሚሆን ሀገራዊ ጥናት መደረጉን ገልጸው፣ በጥናቱ መሠረት በዩኒቨርሲቲው ዋና ዋና የለውጥ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በዚህም መሠረት ከዚህ ቀደም የነበሩ የአካዳሚክ ፕሮግራሞች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እንዲቆሙ ተደርጎ፣ ለፐብሊክ ሴክተሩ ቀጥተኛ አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ አዳዲስ ፕሮግራሞች መቀረጻቸውን ጠቁመዋል።

ከተዘጋጁት 29 ፕሮግራሞች መካከልም 18 የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራሞች በትምህርት ሚኒስቴር ጸድቀው ሥራ ላይ እንዲውሉ መደረጉንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

ለሲቪል ሰርቪሱ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ኮርሶች እንዲሁም የባህሪያዊና ቴክኒካል ብቃት ምዘናዎች በአዲሱ ካሪኩለም ውስጥ መካተታቸውን አስረድተዋል።

የምርምር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ የመንግሥት አሠራርንና አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፣ ችግሮችን በመፍታት ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ መደረጉን ጠቅሰዋል።

የሲቪል ሰርቫንቱን አቅም ለማጎልበት የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ፍላጎቶችን ያገናዘበ የሥልጠና ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም አመላክተዋል።

የሪፎርም ሥራዎቹ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁ፣ ዘመናዊና ውጤታማ የሰው ኃይል የማፍራት ሚናውን በጥራት እንዲወጣ የሚያስችሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የትምህርት አሰጣጥ ሥርዓቱን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቁን ጨምረው አስታውቀዋል።

አዲሱ ሪፎርም በ2019 የትምህርት ዘመን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

ዩኒቨርሲቲው የሪፎርሙ አካል የሆነ የሎጎ ለውጥ ማድረጉንም በዚሁ ወቅት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም