ቀጥታ፡

የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የቀብር ስነ-ስርዓት በአምቦ ከተማ ተፈጸመ

አምቦ ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የአርቲስት እና የሰብአዊ መብት ታጋይ እልፍነሽ ቀኖ የቀብር ስነ-ስርዓት በአምቦ ከተማ ተፈጸመ።

በ1954 ዓ.ም በምስራቅ ወለጋ ዞን ጉቶ ጊዳ ወረዳ የተወለደችው አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ፣ በኪነጥበብ ዘርፍ የነበራትን ፍላጎትና ብቃት ለማሳካት በሐዊሶ ጉደቱ ወለጋ (የወለጋ እድገት የባህል ቡድን) ውስጥ ተቀላቀለች።

በሐዊሶ ጉዳቱ ወለጋ ውስጥም የነበራትን ጀግንነትና ክህሎት በማሳየት ጎልታ ለመታወቅ በቃች።

በኋላም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በዚያ ዘመን ውድ ህይወቷን ሳትሰስት በጣፋጭ ድምጿ ለኦሮሞና ሌሎች ጭቁን ህዝቦች ድምፅ በመሆን እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ የጽናት አርአያ ሆና አልፋለች።


 

በዚህ ባካሄደችው ትግል ውስጥ በርካታ እስራትና እንግልቶችን ያሳለፈች ሲሆን፣ አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ በህይወት ዘመኗ የህዝቦችን አንድነት በመስበክ እራሷን እንደ ሻማ አቅልጣ የኖረች ናት።

አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ከ10 በላይ አልበሞችን ሰርታ ለህዝብ ያቀረበች ሲሆን፣ እነዚህ ዘፈኖቿም የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩና የኦሮሞን ትግል ወደፊት ያስጓዙ ነበሩ።

አርቲስት እልፍነሽ ሁለት ሴት ልጆች ወላጅ እናትና የሌሎች የሁለት ልጆች አሳዳጊ  መሆኗን ከህይወት ታሪኳ ለማወቅ ተችሏል።


 

አርቲስት እልፍነሽ ቀኖ ጳጉሜ 01 ቀን 2018 ዓ.ም በተወለደች በ64 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየች ሲሆን፣  ዛሬ ጠዋት አስክሬኗ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሽኝት ተደርጎለታል።

የአርቲስት እልፍነሽ ቀኖ የቀብር ስነ-ስርዓት የመንግስት ባለስልጣናት፣ ወዳጅ ዘመዶቿና ቤተሰቦቿ፣ አድናቂዎቿ እንዲሁም የአምቦ ከተማ እና የአካባቢው ነዋሪዎች በተገኙበት በአምቦ ከተማ ተፈጽሟል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም