ቀጥታ፡

የፀጥታ ኃይሉ የጸናች ሀገርን ለትውልድ ለማሻገር በትጋት እየሰራ ይገኛል

ባህር ዳር ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የፀጥታ ኃይሉ ለመጪው ትውልድ አስተማማኝና  የፀናች ሀገርን ለማስረከብ  በትጋት እየሰራ መሆኑን በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ገለጹ።

በአማራ ክልል የፅናት ቀን "ፅኑ መሰረት ለማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እና በፓናል ውይይት በባህር ዳር ከተማ ተከብሯል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የአስተዳደር ጉዳዮች ክላስተር አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የጸጥታ ኃይሉ መንግሥትና ሕዝብ የሰጡትን ሀላፊነት በጀግንነት በመወጣቱ የክልሉ ልማት እንዲቀጥል አድርጓል። 

በዚህም ፅንፈኛ ኃይሎችን በፅናት በመመከት የክልሉን ሰላም በቅንጅት ማስፈን መቻሉን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የገጠሟትን ውጣ ውረዶች በቁርጥ ቀን ልጆቿ ፅናት ማለፏን ገልጸዋል። 


 

ይህንንም በትውልድ ቅብብሎሽ በማፅናት ምቹ ሀገርን የመገንባቱ ሥራ የነቃ የዜጎችን ተሳትፎ እንደሚጠይቅ ጠቁመዋል።

የሀገርን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ፣ የክልሉን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር በፅናት መሰራቱን ያነሱት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ሌተናል ጄነራል ጥጋቡ ይልማ ናቸው።


 

በክልሉ ሰላምን በማስከበር ልማትን ለማዝለቅ የጸጥታ ኃይሉ ተልዕኮውን በጀግንነት ለመወጣት ራሱን ዝግጁ ማድረጉንም አስገንዝበዋል።

በዓሉ የጸጥታ ኃይሎች የተለያዩ ትርኢቶችን በማሳየት፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ እና በፓናል ውይይቶች ተከብሯል።

በዝግጅቱም ላይ የአማራ ክልል ጸጥታ ቢሮ፣ የክልሉ ፖሊስ ዋና መምሪያ፣ የክልሉ ሚሊሺያ እና የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ሰራተኞችና የጸጥታ አባላት በጋራ ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም