ቀጥታ፡

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉና የሁለቱ አገራት የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት እንዲጠናከር ጥሪ አቀረቡ።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ካለው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ (AIM Congress) ጎን ለጎን የኳታር ቻምበር የቦርድ አባል አሊ ቢን አብዱላቲፍ አል ሚስናድ ጋር ዛሬ መወያየታቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከሥፍራው ዘግቧል።


 

ውይይቱ የኳታር ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለይም በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በማማከር አገልግሎትና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ተሳትፏቸውን ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በወቅቱ፣ ኢትዮጵያ የውጭ ባለሀብቶችን ለመሳብና ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ ለመፍጠር መንግሥት ትኩረት አድርጎ የሚሠራቸውን ሥራዎች አብራርተዋል።

በዚህም የኳታር ባለሀብቶች በአገሪቱ ያሉትን ምቹና አስቻይ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲጠቀሙና ግንኙነታቸው ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አድርገዋል።


 

የኳታር ቻምበር የቦርድ አባል አሊ ቢን አብዱላቲፍ አል ሚስናድም በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የኳታር ባለሀብቶች በግብርና፣ በጤና፣ በመሠረተ ልማት ግንባታ በተለይም በቤቶች ግንባታና በዲጂታል ልማት ዘርፍ ለመሳተፍ ፍላጎት አላቸው።

በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ የኳታር ባለሀብቶች እንዲጠቀሙበት ለማድረግና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሠሩም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም