ቀጥታ፡

የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለሀገር ሉዓላዊነት በቁርጠኝነት መስራታችንን እንቀጥላለን 

ደሴ ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የአካባቢያችንን ሰላም በመጠበቅ ለሀገር ሉዓላዊነትና ሰላምን ለማጽናት በቁርጠኝነት መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉ በደሴ ከተማ የሚገኙ የፖሊስ አባላት ገለጹ፡፡

የጽናት ቀን የመከላከያ ሰራዊት፣ የፖሊስ፣ የማረሚያ ቤትና ሌሎች የጸጥታ ኃላፊዎችና አባላት በተገኙበት በደሴና በደብረ ብርሃን ከተሞች በድምቀት ተከብሯል።

የከተማዋ ፖሊስ አባል ዋና ሳጅን አባይነህ ተወልደ በዚሁ ወቅት  ፤ ሰላማችንን በመጠበቅ ለሀገር  ሉዓላዊነት እና ሰላምን ለማጽናት በቁርጠኝነት መስራታችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።


 

ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ልማት እስከ ህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ጠቁመው፣ በጽናት ህዝብና ሀገር የጣለባቸውን አደራ እንደሚወጡ ጠቅሰዋል።

ሌላው የፀጥታ አባል መቶ አለቃ ጀማል ኢብራሂም በበኩላቸው፤ ከህዝብ ጋር የጀመርነውን ትስስር በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት በሚደረግው ጥረት ውስጥ የድርሻችንን መወጣታችንን እንቀጥላለን ብለዋል።


 

"ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅና ብሄራዊ ጥቅም መከበር መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁና ቁርጠኛ ነኝ" ያለችው ደግሞ ሌላዋ የፀጥታ አባል የአለምወርቅ አለበል ናት።


 

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ሰይድ አሊ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በከተማዋ ዘላቂ ሰላም መስፈኑ እየተካሔደ ያለውን ልማት ለማፋጠን ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል።


 

በቀጣይም  በቀጠና፣ በብሎክና ሌሎች አደረጃጀቶችን በማጠናከር የመደመር መንግስት ትሩፋቶች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው፤ የፀጥታ መዋቅሩ ከህዝብ ጋር በመተባበር ሰላምን ማስፈን መቻሉ ለልማት ስራው ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል ብለዋል።


 

ይህም የደሴ ከተማ የቱሪዝም፣ የኮንፈረንስና የኢንቨስትመንት ማዕከል እንድትሆን መልካም እድል የሚፈጥር እንደሆነም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ በደብረ ብርሃን ከተማ የፀጥታ ተቋማትና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ የፅናት ቀን በተለያዩ ወታደራዊ ትርኢቶችና ዝግጅቶች ተከብሯል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት፤ የከተማዋን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት በማረጋገጥ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት ከማሳደግ  አንፃር ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ብለዋል።


 

የ105ኛ ኮማንዶ ክፍለጦር አዛዥ ኮሎኔል አሰፋ አየለ በበኩላቸው፤ ሰራዊቱ ከአባቶች የተረከበውን ጀግንነት በመጠቀም የሀገርንና የህዝብን ጥቅምና ክብር ለማስጠበቅ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በጠላት ሴራ የሀገር እድገት እንደማይቆም የመጣንበት መንገድ ማረጋገጫ ነው ያሉ ሲሆን ፣ በተለይ ጫካ ገብተው አፈሙዝ ያነሱ ኃይሎች መንግስት ያቀረበውን የሰላም እድል እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም