የጸናች ሀገርን ለመገንባት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
የጸናች ሀገርን ለመገንባት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ ነው- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ
ወላይታ ሶዶ ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- ሀገራዊ አንድነትና ልማትን በማስቀጠል የጸናች ሀገርን ለመገንባት የዜጎች የነቃ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ ።
ጳጉሜን 3 "የጽናት ቀን" በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ ከተማ ከፍተኛ የክልልና የዞን አመራሮች፣ የፀጥታ አካላት፣ የመንግሥት ሠራተኞችና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።
በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት፤ የጽናትን ቀን ስናከብር ጀግኖች አባቶች ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት የከፈሉትን ታሪካዊ መስዋዕትነት በልማት ለመድገም ዳግም ቃል የምንገባበት ነው።
ወቅቱ የድህነትና የኋላ ቀርነት ታሪክን በዘላቂነት ለመቅረፍ በጽናት የመቆሚያና አባቶች ለሀገር ያደረጉትን ተጋድሎ የምናስብበት ነው ሲሉም አመልክተዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የሰላምና ጸጥታ አካላት ለኢትዮጵያ ሰላም እና ጽናት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ ምስጋና የሚቀርብበት ዕለት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍስሃ ጋረደው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽና በልጆቿ ጀግንነት የጸናች ታላቅ ሀገር መሆኗን ገልጸዋል።
የጽናት ቀን እጅ ለእጅ በመያያዝ የክልሉን ሰላም ይበልጥ በማጽናት የተጀመሩ ልማቶችን ወደ ላቀ ውጤት ለማድረስ በቁርጠኝነት የሚሰራበት መሆኑን አስገንዝበዋል።
የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ረዳት ፕሮፌሰር ሳሙኤል ተሰማ በበኩላቸው፣ ሀገር የማጽናትና የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ ዳር የማድረስ ሥራ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ አቅም እንደሚጠይቅ ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁላችንም በልማት ሥራዎች ላይ ይበልጥ በባለቤትነት ስሜት መሳተፍ ይገባናል ብለዋል።
በመተባበር ለሕዝብ ተጠቃሚነት በቅንነት በመሥራት ጀግኖች አባቶች በደማቸው ጠብቀው ያስተላለፉልንን ሀገር ማጽናት የትውልድ አደራ ነው ሲሉም አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ያጋጠሟትን በርካታ ፈተናዎች በጽናትና በጀግንነት በማለፍ የማትበገር እንድትሆን መስዋዕት የከፈሉ ጀግኖችን ታሪክ በልማት መድገም ይገባል ያሉት ደግሞ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ እታገኝ ኃይለማርያም ናቸው።
አባቶች በከፈሉት ተጋድሎ የተረከብናትን ሀገር የመጠበቅና አጽንቶ ለትውልድ ማስተላለፍ ዋነኛ ተግባር ነው ብለዋል።
ለከተማችን ዘላቂ እድገት በመስራት የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማጽናት በጋራ መቆም ይገባል ሲሉም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በበአሉ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ፣ የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብረመስቀል ጫላን ጨምሮ ከፍተኛ የክልል፣ የዞንና የወላይታ ሶዶ ከተማ አመራሮች፣ የፀጥታ ኃይሎችና በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።