ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የሀገራችንን ሉዓላዊነት እናስጠብቃለን -ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ - ኢዜአ አማርኛ
ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር የሀገራችንን ሉዓላዊነት እናስጠብቃለን -ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ
ሰመራ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- ያጋጠሙንን ፈተናዎች በፅናት በመሻገርና ወደ መልካም ዕድል በመቀየር፣ የሀገራችንን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም በፅናት እናስከብራለን ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።
የፅናት ቀን "ፅኑ መሰረት፣ብርቱ ሀገር" በሚል መሪ ሐሳብ በሠመራ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ታጅቦ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ፤ ተከብራ የኖረችውን ሀገራችንን ያጋጠሟትን ፈተናዎች በፅናት በመሻገርና ወደ ዕድል በመቀየር ሉዓላዊነቷን እናስጠብቃለን ብለዋል።
ሀገራችን በተለያዩ ዘመናት በርካታ ፈተናዎችን ተቋቁማና ተጋፍጣ አልፋለች ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ታሪካዊ ጠላቶቿንም አንገት በማስደፋትና እፍረት በማከናነብ የመለሰች መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር ሕዝብም የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ ከሀገር መከላከያ ሰራዊትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ታሪካዊ ሚናውን መወጣቱን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህ ክልላዊና ሀገራዊ አደራ አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሁመድ በበኩላቸው፤ የሰላምና የፀጥታ ተቋማት ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት በመስራት የሰላም ዘብነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
ሰላማችንን ለማጠናከርና ለማስጠበቅ ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች በፅናት በመሻገር፣ ተቋማዊ ቅንጅትን በማጠናከርና የኅብረተሰቡን ተሳትፎ በማሳደግ የሕግ የበላይነትን የምናስከብር ሕዝቦች ነን ሲሉም ተናግረዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ምሰራቅ ዕዝ አባላት ሀገራችንን በፅናት ጠብቀው ያስረከቡንን የአባቶቻችንን አደራ በመረከብ፣ ዳር ድንበሯን እና ሉዓላዊነቷን አስከብረን ለሚቀጥለው ትውልድ ለማሻገር ዝግጁ ነን ብለዋል።
ከሰራዊቱ አባላት መካከል ሻምበል ቀረ ዓለም አዱኛ እንደገለጹት፤ ሀገራችን በጀግኖች ልጆቿ የውጭ ወረራዎችንና ትንኮሳዎችን በመመከት ለዘመናት በፅናት እና በአንድነት እንድትቆም ተደርጋለች።
እኛም የተሰጠንን ግዳጅ በመፈፀም በቁርጠኝነት ተጋድሎ የፀናች አገርን ሰላምና ልማቷን ለማስቀጠል በፅናት እንታገላለን ብለዋል።
ምክትል መቶ ዓለቃ ዘውድነሽ ንጉሱ በበኩላቸው፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ማስከበር ከፍተኛ መስዋዕትነት የተከፈለበት እና ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም ያለው ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
አባቶቻችን አጥንታቸውን ከስክሰው፣ ደማቸውን አፍስሰው ያስከበሩልንንና የትኛውንም ፈተና አልፋ ጸንታ የቆየችውን ሀገር ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት እኛም በፅናት ቆመን እናስከብራለን ብለዋል።
የተረከቡትን አደራ በመወጣት ሀገሪቱን ለቀጣዩ ትውልድ ለማሻገር በፅናት መቆማቸውን የተናገሩት ደግሞ ምክትል አስር ዓለቃ ወንዶሰን ኃይሉ እና አስር ዓለቃ ተካ ዓለሙ ናቸው።