ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል
ወልቂጤ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የጉራጌ ዞን አስተዳደር በወልቂጤ ከተማ በ1 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያስገነባውን ባለ ዘጠኝ ወለል የአስተዳደር ሕንጻ ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እንደገለፁት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው ለአገልግሎት እየበቁ ይገኛሉ።
ይህም የህዝብ ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አንጻር ጉልህ ሚና እየተጫወተ በመሆኑ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ በጥራትና በፍጥነት የማጠናቀቅ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በክልሉ በዕቅድ የሚመራና በፅናት የሚሰራ አመራርና ሠራተኛ በየደረጃው በመኖሩ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጥራት እና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ዛሬ ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃው የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕንጻ ለእዚህ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕንጻው አስተዳደሩ ለህብረተሰቡ የሚሰጠውን አገልግሎት በማዘመንና በማቀላጠፍ በኩል ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ የልማት ሥራዎች ላይ የህብረተሰቡ ተሳትፎ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ጉራጌ ዞን በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና እንዲሁም በፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄ ግንባር ቀደም ተሳትፎ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው፤ በመደመር መንግስት እይታ ፈተናዎችን በመቋቋም የነገን ትውልድ ጭምር ታሳቢ ያደረጉ ፕሮጀክቶች እውን እየተደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።
ለዚህም በ2 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈውና ለምረቃ የበቃው ባለዘጠኝ ወለል የጉራጌ ዞን አስተዳደር ሕንጻ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ ሕንጻው ዘመኑን ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
በዞኑ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫዎችን በማስፋፋት ለህብረተሰቡ ጊዜና ወጪን የሚቆጥብ ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት የተጀመረው ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
በዞኑ የአስተዳደር ሕንጻ ምረቃ ሥነስርዓት ላይ ከፌደራል፣ ከክልል እና ከአጎራባች ዞንና ልዩ ወረዳዎች የመጡ የሥራ ሃላፊዎችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።