ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ ስኬት የኢትዮጵያውያን የጽናት ውጤት ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሕዳሴ ግድብ የተገኘው ስኬት በመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረት፣ ጽናትና ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሕዳሴ ግድብ ግንባታን በውጤታማነት ለማጠናቀቅ የሕዝብ ተሳትፎን በማስተባበር በኩል ልዩ ልዩ ተግባራትን ሲያከናወኑ የቆዩ አካላትን የማመስገንና የእውቅና መርሃ ግብር ተካሄዷል።


 

ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር አስፋው ዲንጋሞ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም የአባይን ውኃ ለልማትና ለሀገራዊ ጥቅም ለማዋል ያደረጉት ጥረት ትልቅ ውጤት አስገኝቷል።

የግድብ ግንባታ የኢትዮጵያውያን የጋራ ጽናትና ተሳትፎ ማሳያ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

በግድቡ ግንባታ ሂደት መላው ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖረው ዳያስፖራ በገንዘብ፣ በእውቀትና በሞራል እንዲሁም በተለያየ መልኩ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የትውልድ አደራ፣ የሉዓላዊነታችን ማረጋገጫና የኢትዮጵያውያን የጋራ ጽናት ማሳያ ፕሮጀክት ነው ሲሉም ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


 

የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሞራል፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣ በአካባቢ ጥበቃና በሕዝብ ዲፕሎማሲ ያደረጉት ተሳትፎ ግድቡ እውን እንዲሆን ወሳኝ ሚና እንደነበረው ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ የኢትዮጵያውያን የጋራ ርብርብ ማዕከል ሆኖ መቆየቱን ጠቁመው፣ ሕዝቡ በጋራ በመቆም ለስኬት ማብቃቱንም አስታውሰዋል።

የሕዝብ ተሳትፎ ከገንዘብ ማሰባሰብ ባሻገር የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም ማስረዳት ላይ የጎላ ሚና እንደነበረውም ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል በግድቡ ግንባታና በሕዝብ ተሳትፎ ሂደት የተከናወኑ ተግባራት፣ ያጋጠሙ ፈተናዎችና የተገኙ የድል ታሪኮችን የሚዘክር "ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የፅናት ተምሳሌት" የተሰኘ ባለ199 ገጽ መጽሐፍ በመርሃ ግብሩ ተመርቋል።

መጽሐፉ የሕዳሴ ግድብን ለማሳካት የተደረገውን ትግል፣ የሕዝቡን ተሳትፎና የጋራ ጥረት በማስመዝገብ ለቀጣዩ ትውልድ ታሪካዊ ማስታወሻ ሆኖ እንዲያገለግል መዘጋጀቱም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም