በመጪዎቹ በዓላት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በመጪዎቹ በዓላት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን የማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-በመስከረም 2019 ዓ.ም ለሚከበሩ በዓላት ለህብረተሰቡ አስፈላጊውን ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በመሆን በመስከረም 2019 ዓ.ም የሚከበሩ የዘመን መለወጫ፣ መስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላትን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተፈራ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መጪዎቹን በዓላት የ90 ቀናት ዕቅድ አካል በማድረግ ከከተማ እስከ ወረዳ ድረስ ግብረ ኃይል በማቋቋም ለሕብረተሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ዝግጅቱ ለሕብረተሰቡ አስተማማኝ የውኃ፣ ኤሌክትሪክ እና ሌሎች ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶችን መስጠት፣ አደጋን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።
የእሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ቴዎድሮስ ወልደሚካኤል፤ እሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር በዓሉን ለማክበር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና አደጋዎች ሲያጋጥሙ በ939 ነፃ የጥሪ ማዕከል ጥቆማ እንዲሰጥ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሞገስ አርጋው፤ የውኃ አቅርቦትን ተደራሽ ለማድረግ የተሰበሩ መስመሮች ጥገና ተደርጎላቸዋል ብለዋል።
ሕብረተሰቡ ከውኃና ፍሳሽ ጋር የተያያዘ ማንኛውም ችግር ቢገጥመው በ906 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችል ተናግረዋል።
ለሕብረተሰቡ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የመስመር ጥገናና ማሻሻያ መደረጉን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአዲስ አበባ ሪጅን ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ጂሳ ካሳ ናቸው።
የተቋሙ አገልግሎት መስጫና የካርድ መሙያ ቢሮዎች በበዓል ዋዜማና ዕለት ቀኑን ሙሉ አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቅሰው፤ ለጥያቄና ማብራሪያዎች በ905 ነፃ የጥሪ ማዕከል መጠቀም ይችላሉ ብለዋል።
የከተማዋ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ቆሻሻን ለመሰብሰብና የከተማዋን ጽዳት ለመጠበቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን በመጠቆም፤ ሕብረተሰቡ በዓሉን ቆሻሻን በአግባቡ በመያዝ የከተማዋን ውበት በመጠበቅ ማክበር እንዳለበት አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መብራት አገልግሎት አስተዳደር ባለሥልጣን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዮሐንስ ለገሰ በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡ በከተማዋ የ24 ሰዓት አገልግሎት ለመስጠት የተዘረጉ ምቹና ዘመናዊ የመብራት መሠረተ ልማቶች እንዳይጎዱ በመጠበቅ በዓሉን እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል።