ሀገራዊ የዲጂታል ደም መረጃ ስርዓት መተግበሪያው የለጋሾችን እርካታ የሚጨምር ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ የዲጂታል ደም መረጃ ስርዓት መተግበሪያው የለጋሾችን እርካታ የሚጨምር ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት ይፋ ያደረገው የዲጂታል ደም መረጃ ስርዓት መተግበሪያ የለጋሾችን እርካታ እንደሚያጠናክር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ ባንክ አገልግሎት «አድን» (AEBIS) የተሰኘ ሀገራዊ የዲጂታል ደም መረጃ ስርዓት መተግበሪያ ይፋ አድርጓል።
ዲጂታል መተግበሪያው ከለጋሽ ምዝገባና የደም ልገሳ፣ የላቦራቶሪ ምርመራ፣ የደም ክፍሎች ዝግጅት፣ ከክምችት አስተዳደር እስከ ስርጭት ድረስ ያሉ ዋና ዋና የደም አገልግሎት ሂደቶችን በአንድ የዲጂታል መረጃ ስርዓት ለማገናኘት የተዘጋጀ መሆኑ ተመላክቷል።
ሀገራዊ የዲጂታል የደም መረጃ ስርዓቱ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃን በማቅረብ፣ የደም አገልግሎት ክትትል በማጠናከር፣ የጥራትና ደህንነት ስርዓትን በማሻሻል እንዲሁም በመረጃ የተደገፈ ውሳኔ አሰጣጥን በማጎልበት በኩል ጠቀሜታው ከፍ ያለ መሆኑም ተገልጿል።
ይፋ በማድረጊያ መርሃ ግብሩ የተገኙት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ የማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቅሰሙ ማሞ እንዳሉት፤ የዲጂታል የደም መረጃ ስርዓቱ እንደ ሀገር የለጋሾችን እርካታ ያጠናክራል።
በመሆኑም ይፋ የሆነው የዲጂታል ሲስተም ቀጣይነት እንዲኖረው በትኩረት መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ተወካይ መብራቱ ማሴቦ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዛሬ ይፋ የሆነው አድን (AEBIS) ዲጂታል የደም መረጃ ስርዓት እንደ ሀገር ትልቅ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ስርዓቱ የኢትዮጵያን የዲጂታል 2030 ስትራቴጂ ጉዞ ማሳያ እንዲሁም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ ሕዋስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አሸናፊ ታዘበው (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ይፋ የተደረገው አድን ኢትዮጵያ የተሰኘ የደም መረጃ ስርዓት ከመጀመሪያው ልገሳ እስከ ተቀባዩ ታካሚ ድረስ ያሉ የደም አገልግሎቶችን በአንድ የጋራ መረጃ ስርዓት መከተል የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰላሳ አምስት የሚሆኑ የደም ባንኮች ከአድን ኢትዮጵያ የመረጃ ስርዓት ጋር መገናኘታቸውንም ተናግረዋል።
አድን ኢትዮጵያ ዲጂታል የደም መረጃ ስርዓት የለጋሽ ምዝገባና አስተዳደር፣ የልገሳ መረጃ አደረጃጀትን፣ የምርመራና የማቀነባበሪያ ሂደቶችን ተከታታይነትና የጥራት አመራርን፣ በተለይም በመረጃ ላይ የተመሰረተ የደም መረጃ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል ነው ያሉት።