በሁሉም መስኮች እያንሰራራች ያለችው ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ በጀግኖች ልጆቿ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም መስኮች እያንሰራራች ያለችው ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ በጀግኖች ልጆቿ ተጠናክሮ ይቀጥላል - አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ
ወልቂጤ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-በሁሉም መስኮች እያንሰራራች ያለችው ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ሉአላዊነቷ ጸንቶ የጀመረችው የብልጽግና ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ ገለጹ።
የጽናት ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ በወልቂጤ ከተማ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) እና የተለያዩ የጸጥታ አካላት በተገኙበት ተከብሯል።
የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋጤ ሰርሞሎ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ በመደመር መንግስት ኢትዮጵያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች በፅናት በማለፍ አኩሪ እና እምርታዊ ውጤቶችን ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያን የአፍሪካ ተምሳሌት ለማድረግ የሚያስችሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን በስኬት ማከናወን መቻሉንም አፈ ጉባኤዋ አመልክተዋል።
በተለይም የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የተወሰዱ አዳዲስ ኢንሼቲቮችና ውጤታማነቱ በግልጽ እየታየ ያለው የኮሪደር ልማት የሀገሪቱን የልማት ምዕራፍ በአዲስ መልክ የቀየሩ መሆናቸውንም ነው የገለጹት።
እነዚህና የተጀመሩ አበይት የልማት ተግባራት ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ በጠንካራ መሰረት ላይ ሆና እያንሰራራች መሆኗን ተጨባጭ ማሳያዎች ናቸው ብለዋል።
በሁሉም መስኮች ውጤት እያስመዘገበች ያለችው ኢትዮጵያ ሉአላዊነቷን በፅናት አረጋግጣ ወደፊት የምታደርገውን የብልጽግና ጉዞ አጠናክራ እንደምትቀጥልና ለእዚህም ትውልዱ የራሱን አዲስ ታሪክ በመስራት የአባቶቹን ጀግንነት ማስቀጠል አለበት ብለዋል።
የሚያጋጥሙ ማናቸውንም ችግሮች ተቋቁሞ የብልጽግና ጉዞን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ሀገራዊ አንድነት፣ ሰላምና ፅናት ወሳኝ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አመላክተዋል።