ቀጥታ፡

በልጆቿ ፀንታ የኖረች ሀገር

በብርሀኑ ፍቃዱ  (ሰቆጣ ኢዜአ)

የውጪ ወራሪን  በጀግኖች አባቶቻችን ክቡር መስዋዕትነትና በጸና ተጋድሎ በማክሸፍ፣ ኢትዮጵያን በትውልድ ቅብብሎሽ አጽንቶ አሁን ላለንበት ማድረስ ተችሏል።

ለአብነትም የጣሊያን ወራሪ ኃይል በጥንት አባቶቻችን ተጋድሎ ሽንፈትን ተከናንቦ መመለሱ ለኢትዮጵያዊያን ድልና  ለመላው ጥቁር ህዝብ  የነፃነት ፋኖስ ሆኖ ሲዘከር ይኖራል።

"የአይቻልም" መንፈስን በ"ይቻላል" ለውጠው ያሳዩት እነዚህ ጀግኖች፣ ለጥቁር ህዝቦች የነፃነት ጮራ የፈነጠቁ፣ እኩልነትን ያበሰሩ፣ የሀገር ፍቅርና ጽናትን ለልጅ ልጆቻቸው ያወረሱ እንዲሁም ታሪክን በወርቅ ቀለም የጻፉ ናቸው።

 የዛሬው ባለታሪኮቻችን ሻለቃ ባሻ ሞገስ የማነብርሃን እና መቶ አለቃ አበባው ገብረ እግዚአብሔር ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መከበር በጽናት ታግለው ያሳለፉትን የተጋድሎ ታሪክ «የጽናት ቀን»ን ምክንያት በማድረግ እንደሚከተለው እናስቃኛችኋለን።

 በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሰቆጣ ወረዳ «ቃፋ ሚካኤል» በተባለ መንደር ነዋሪ የሆኑ ሻለቃ ባሻ ሞገስ የማነብርሃን፣ ከ1960 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 ዓመታት ክቡር በሆነው የውትድርና ሙያ ሀገራቸውን አገልግለዋል።

 "ጀግንነትን፣ አሸናፊነትን እና ለሀገር አንድነት መስዋዕት መክፈልን ከአባቴ ከሻለቃ የማነብርሃን የወረስኩት አኩሪ ታሪክ በመሆኑ፣ እኔም ለሀገሬ ክብር በጽናት ተዋድቄያለሁ" ሲሉ ይገልጻሉ።

 የውትድርና ሕይወታቸውን በቀብሪ ደሃር ማሰልጠኛ ማዕከል የጀመሩት ሻለቃ ባሻ ሞገስ፤ በዳሎል፣ ምፅዋ፣ ከረን፣ ሙሳቤት፣ ቃሮራ፣ አፋበት፣ ናቅፋ እና በሌሎች የኤርትራ ቆላማና ደጋማ አካባቢዎች የተሰጣቸውን ግዳጅ በጽናት ተወጥተዋል።

 "የወጣትነት እድሜዬን ክቡር የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል ሀገር የሰጠችኝን ግዳጅ በጽናት ተወጥቻለሁ" ያሉት ሻለቃ ባሻ ሞገስ፤ ሀገርን በውትድርና የማገልገል እድል ማግኘት ታላቅ ዕድልና ክብር መሆኑን ገልጸዋል።

 ኢትዮጵያን የመሰለች ጥንታዊት ሀገር ሉዓላዊነቷ፣ አንድነቷና ክብሯ እንዲጠበቅ አባቶቻችንም ሆኑ እኛ ዋጋ ከፍለናል፤ የአሁኑ ትውልድም ሉዓላዊነቷን አጽንቶ ለመዝለቅ ወቅቱ የሚጠይቀውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዘብ መቆም አለበት ሲሉ ይመክራሉ።

አሁን ያለው የሀገር መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል አቅምና ትጥቅ፣ ከሳይበር እስከ መካናይዝድ ልቆ የተደራጀ በመሆኑ ከኢትዮጵያ አልፎ ለቀጠናው ዘብ የሚሆን አስተማማኝ ኃይል መሆኑን እያየን ነው ብለዋል።

"ሀገራችን የባሕር በር አልባ መሆኗ ያስቆጨኛል፤ ዕድሜ ልኬን ለሀገሬ ዘብ ብቆም ምኞቴ ነው" ያሉት ሻለቃ ባሻ ሞገስ፤ ወጣቱ ትውልድ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ የተጀመረውን ተግባር በሰላማዊ መንገድ ለማሳካት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።


 

 ሌላው የከተማዋ ነዋሪ መቶ አለቃ አበባው ገብረ እግዚአብሔር በበኩላቸው፤ «ታላቋን ሶማሊያ» ለመመስረት በሚል በጦር የሰከረው የዚያድ ባሬ መንግሥት በእብሪት ተነሳስቶ ሀገራችንን በወረረበት ወቅት በ18 ዓመታቸው የቀድሞውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀላቸውን ያወሳሉ።

 "ወላጅ አባቴ  የሀገር መከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አባል ነበር" ያሉት መቶ አለቃ አበባው፤ እሳቸውና ታናሽ ወንድማቸው የአባታቸውን አሻራ በመከተል የመከላከያ ሠራዊቱን መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።

 የ10ኛ፣ 19ኛ፣ እና 82ኛ ልዩ ኮማንዶ ክፍለ ጦሮች አባል በመሆን በሕክምና ሙያቸው ሠራዊቱን ለ12 ዓመታት ማገልገላቸውን ጠቁመው፤ ውትድርና ጽናትን፣ የሀገር ፍቅርን እና ከራስ በፊት ለወገን መስዋዕት መሆንን የሚጠይቅ የተከበረ ሙያ መሆኑን ገልጸዋል።

ከሰራዊት አባልነት ከተገለሉም በኋላ  ባካበቱት የሕክምና ሙያ በሰቆጣ ጤና ጣቢያና በተፈራ ኃይሉ ሆስፒታል ተቀጥረው ህዝባቸውን ያገለገሉ ሲሆን፣ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ በመሆንም ሰርተዋል።

 "ለዘመናት ያዘንኩበት የባሕር በር ጉዳይ አሁን ላይ የትውልዱና የመንግሥት አጀንዳ ሆኖ መነሳቱ አስደስቶኛል" ያሉት መቶ አለቃ አበባው፤ ይህም የሀገራችንን የቀደመ ገናናነት የሚመልስ በመሆኑ ለስኬቱ በአንድነት መሰለፍ ይገባል ብለዋል።

 የአሸናፊነትና የጀግንነት ወኔ ከጥንት ጀምሮ ያለና የሚቀጥል መሆኑን አሁን ላይ  የመከላከያ ሠራዊት ዘመኑን የዋጀ አደረጃጀትና የቴክኖሎጂ አቅም በማየት መገንዘብ ይቻላል ብለዋል።

 ወጣቱ ትውልድ ጸንታ የተከበረች ሀገሩን በአንድነትና በፍቅር ሉዓላዊነቷን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት መክረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም