ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን ጽናት በርካታ ድሎችን ያጎናጸፈ ነው-ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ጳጉሜን 3 /2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያውያን ጽናት እና አይበገሬነት በርካታ ድሎችን እንዲጎናጸፍ አድርጓል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

በክልሉ የጽናት ቀን በወታደራዊ ትርኢትና በተለያዩ ዝግጅቶች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የፀጥታ ኃይሎች እና ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተከብሯል።


 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን በወቅቱ ባስተላለፉት መልእክት፣ በኢትዮጵያውያን ጽናትና አይበገሬነት ሀገሪቱ የሚያጋጥሟትን ፈተናዎች በድል አድራጊነት እንድትወጣ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ያለማንም ድጋፍ እና ዕገዛ በማጠናቀቅ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ማከናወን የድል አድራጊነት መገለጫ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ለአብነትም በሕዳሴ ግድብ ስኬታማነት የታየውን ጽናት አንስተዋል።

የአሁኑ ትውልድም የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በማስጠበቅ ብሔራዊ ጥቅሟ የተረጋገጠ እና የተከበረች ሀገር ሆና እንድትቀጥል ሁሌም ዝግጁ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።


 

ትውልዱ የተጀመሩ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳድር ሥራዎችን በማጠናከር ለሁለንተናዊ ብልጽግና የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሰላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ በበኩላቸው፣ የጽናት ቀን በተስፋ የመቆም፣ በጋራ የመሥራትና የተሻለ ነገን ለመገንባት ጥንካሬን የምናድስበት ነው ብለዋል።

የብልጽግና ጉዞን እውን ለማድረግ ሰላምን ማረጋገጥ ወሳኝ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም