ቀጥታ፡

ትውልዱ ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ጀግንነት በመድገም ድህነትን ድል ለማድረግ መትጋት አለበት- ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

ቦንጋ፣ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-ትውልዱ ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ጀግንነት በማስቀጠል ድህነትን ድል ለማድረግ መትጋት አለበት ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጳጉሜን-3 "የጽናት ቀን" በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ደረጃ በቦንጋ ከተማ መሃል አደባባይ በድምቀት ተከብሯል።


 

በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ሀገራችን ኢትዮጵያ በየዘመኑ ከውስጥና ከውጭ በርካታ ጠላቶች ቢነሱባትም ጀግኖች ልጆቿ ድል ነስተው ፀንታ እንድትቆይ አድርገዋል።

ቀደምት አባቶችና እናቶች ያለምንም ልዩነት በአንድነት ቆመው የውጭ ወራሪ ጠላቶችን አሳፍረው በመመለስ አድዋን የመሳሰሉ ታላላቅ ድሎችን ማስመዝገባቸውንም አስታውሰዋል።

የአሁኑ ትውልድም የቀደምት አባቶቹን ፈለግ በመከተል የሀገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ከማስጠበቅ በተጨማሪ እንደ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በማሳካት የአይቻልም አስተሳሰብን የቀየረ ታሪክ መስራቱን ገልጸዋል።  

ትውልዱ በልማት ላይ እያስመዘገበ ያለውን ይህን ድል አጠናክሮ በማስቀጠል ከጥንት አባቶቹ የወረሰውን ጀግንነት መድገምና ድህነትን ታሪክ በማድረግ የራሱን አዲስ ደማቅ ታሪክ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

ለእዚህም ልዩነትን በማስወገድ ሕብረብሔራዊነትን ከማጠናከር ባለፈ አንዳችን ለሌላችን መመኪያ መሆን አለብን ሲሉም አስገንዝበዋል።


 

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገሩ ሰላምና ሉአላዊነት፣ ጽናትና ዳርድንበር መከበር በጀግንነት ለከፈለውና እየከፈለ ያለው ዋጋ ሁሌም ሲዘከር ይኖራል ያሉት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ ለዚህም ታላቅ ክብርና ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።

የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ደመላሽ ንጉሥ በበኩላቸው ቀደምት ጀግኖች በብሔር፣ በቋንቋና በሃይማኖት ሳይለያዩ በጋራ ቆመው ሀገርን ከነክብሯ ማቆየታቸው የሀገር ወዳድነትና የጽናታቸው ማሳያ ነው ብለዋል።

የዛሬው ትውልድም የቀደምት ጀግኖችን አኩሪ ገድል በመከተል ድህነትንና ተረጂነትን ለማስቀረት በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማነቱን በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ሚናውን ማጠናከር አለበት ብለዋል ።

ከሀገር የሚበልጥ ምንም ነገር ስለሌለ ያለባቸውን ሀገራዊ ሃላፊነት በጽናትና በቁርጠኝነት እንደሚወጡ የገለጹት ደግሞ  የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ኢንስፔክተር ታማኝ ብሩ እና ረዳት ኢንስፔክተር ኪዳነ ክፍሌ ናቸው። 

ለሀገር ፀንታ በመቆም በየዘመኑ መሰዋዕትነት ለከፈሉና እየከፈሉ ላሉ የሠራዊት አባላት ክብር እንደሚገባ ገልጸው፣ እነሱም 

ለሀገርና ለህዝብ ሲሉ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የፅናት ቀን በዚህ መልክ መከበሩ ለሠራዊቱ ጥንካራ ይሆናል ያሉት የፖሊስ አባላቱ፣ ለወጣቱም ትልቅ መልዕክት እንደሚያስተላለፍ አመልክተዋል፡፡

በበዓሉ ላይ የጸጥታ አካላት፣ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎችና የመንግስት ሠራተኞችም የተሳተፉ ሲሆን በተሰማሩበት ውጤታማ በመሆን ለሀገር ሰላምና እድገት የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም