ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም አጽንቶ መዝለቅ አለበት-የጀግኖች አርበኞች ማህበር - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቱ ትውልድ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም አጽንቶ መዝለቅ አለበት-የጀግኖች አርበኞች ማህበር
ደሴ፤ ጳጉሜን 3/2018(ኢዜአ)፡- ወጣቱ ትውልድ አንድነቱን ጠብቆ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ብሄራዊ ጥቅም ሊያጸና እንደሚገባ የደቡብ ወሎ ዞን ጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ፀሐፊ ተተኪ አርበኛ አየለ ወልደ ጊዮርጊስ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ሉዓላዊነቷ ተጠብቆ የዘለቀችውን ኢትዮጵያ ወጣቱ ትውልድ አንድነቱን አጽንቶ ለመጪው ትውልድ የማስተላለፍ ሕዝባዊና አገራዊ ኃላፊነት ተጥሎበታል።
ወጣቱ አሁን ላይ የተፈጠሩ መልካም እድሎችን በማጽናት ለሕዝብ ተጠቃሚነት፣ ለሀገር እድገትና ዘላቂ ሰላም መስራት እንደሚገባው ፀሐፊው ተናግረዋል።
ሌላው የማሕበሩ አባል ተተኪ አርበኛ ሀምሳ አለቃ ባለሟል መለሰ በበኩላቸው፣ ትውልዱ የአባቶቹን ታሪክና ገድል በማስቀጠል ኢትዮጵያን በማጽናት ማስቀጠል እንደሚገባው አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ፈተና ቢገጥማትም ፈተናውን በጽናት ተቋቁማ ስኬታማ ጉዞዋን ማስቀጠሏ ታላቅ ተምሳሌት መሆኑን ጠቁመው፣ ለዚህም የአባቶቻችን የጀግንነት አስተዋጽኦ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው ብለዋል።
አሁንም ለሀገራችን ሁለገብ እድገት ጸንተን በጋራ በመቆም፣ የተጀመሩ አበረታች ውጤቶችን ማስቀጠል ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።
ትውልዱ አንድነቱንና ሰላሙን በመጠበቅ የኢትዮጵያን የከፍታ ጉዞ ሊያጸና ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የማህበሩ አባል ሀምሳ አለቃ አለማየሁ አበበ ናቸው።
ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ አንድነት ጸንታ፣ ተከብራና ታፍራ የቆየች ሉዓላዊት ሀገር መሆኗን ጠቁመው፣ ትክክለኛ ታሪኳን ወጣቱ ትውልድ በውል ተገንዝቦ እድገቷን ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።