ቀጥታ፡

የፅናት ቀንን ስናከብር ከአባቶቻችን የተረከብነውን አደራ ከዳር ለማድረስ ዳግም ቃላችንን በማደስ ነው - ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ

ቢሾፍቱ፤ ጳጉሜን 3/2018(ኢዜአ ):-የፅናት ቀንን ስናከብር ከአባቶቻችን የተረከብነውን አደራ ከዳር ለማድረስ ዳግም ቃላችንን በማደስ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ገለፁ።

ጳጉሜ 3 'የፅናት ቀን' በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በቢሾፍቱ ስታዲየም በተለያዩ ስነ-ስርዓቶችና ወታደራዊ ትርዒት በደማቁ ተከብሯል።


 

የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ የጽናት ቀን ሀገራችን በአባት አርበኞች ተጋድሎ ለአሁኑ ትውልድ እንድትበቃ ያደረገ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

ባንዳዎችና ባዳዎች የሀገራችን አንድነት እንዲላላና በልማት ወደኋላ እንድትመለስ ለማድረግ ብዙ ጥረቶች ሲያደርጉ እንደነበር የጠቀሱት ኮሚሽነር አራርሳ፤ የጽናት ተምሳሌቱ ጀግናው የሀገር መከላከያ ሳራዊታችን እና መላው የፀጥታ አካላት የውስጥና የውጭ ጠላቶችን ተልዕኮ በማክሸፍ ሀገር እያሻገሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ማንኛውም ኃይል ኢትዮጵያን መድፈር አይችልም ያሉት ኮሚሽነር አራርሳ፤ ለዚህም የሀገር መከላከያ ሠራዊቱንና የፖሊስ ኃይሉን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በማደራጀት ዘርፈ ብዙ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ሠራዊትና በየደረጃው የሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮችም የክልሉ ሰላም አስተማማኝ እንዲሆን እንዲሁም ልማትና ዕድገቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ ረገድ እየተወጡ ያሉት የማይተካ ሚና ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዛሬው ዕለትም ቀኑን ስናከብር ከአባቶቻችን የተረከብናትን ኢትዮጵያ ለማጽናት፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት በማረጋገጥ የሀገራችንን ከፍታና ብልጽግና እውን ለማድረግ ቃል በመግባት መሆኑን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ገልጸዋል።


 

ኮሚሽነር አራርሳ አክለውም፤ ቀኑ ድህነትን ታሪክ በማድረግ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ዳግም ቃል የምንገባበት፣ የጠላትን ከንቱ ምኞት የምናክሽፍና ለሕዝብ የተገባውን ቃልና ጽናት በተግባር ለማረጋገጥ የሚያስችል ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው፤ የጽናት ቀንን ስናከብር እንደ ክልልም ሆነ በሀገር ደረጃ  ዘላቂ ሰላምን አስተማማኝ በማድረግ መሆን እንደሚገባው ገልጸዋል።

ከንቲባ  አለማየሁ አሰፋ አክለውም፤ ቢሾፍቱ የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ከተማ በመሆኗ አስተማማኝ ሰላሟን በማረጋገጥ፣ የተጀመረውን ሁለንተናዊ ልማት አጠናክሮ በመቀጠልና ቃልን በማደስ ቀኑን ማከበር ታሪካዊ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም