ጽናት የልማት፣ የህልውናና የሉዓላዊነት እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የምንከፍለው የማይናወጥ የቁርጠኝነት ልኬት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ - ኢዜአ አማርኛ
ጽናት የልማት፣ የህልውናና የሉዓላዊነት እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የምንከፍለው የማይናወጥ የቁርጠኝነት ልኬት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ
ሐረር፤ ዻጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፦ “ጽናት” የልማት፣ የህልውናና የሉዓላዊነት እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የምንከፍለው የማይናወጥ የቁርጠኝነት ልኬት ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።
ዻጉሜን 3 “የጽናት” ቀን በሐረሪ ክልል ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይም የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የመከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የጸጥታ አካላት የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች ተገኝተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በወቅቱ እንዳሉት ለተለያዩ ፈተናዎች ሳንበገር ዛሬ ለደረስንበት ስኬት ዋንኛው ሚስጥር በጽናት መስራትና መታገል ነው ብለዋል።
በዚህም ታላላቅ ድሎችን እና ስኬቶችን ማስመዝገብ በመቻላችን የህዝባችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ችለናል ነው ያሉት።
“ጽናት” የልማት፣ የህልውናና የሉዓላዊነት እሴቶቻችንን ለማስቀጠል የምንከፍለው የማይናወጥ የቁርጠኝነት ልኬት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመሸሽ ሳይሆን በድፍረት በመጋፈጥ ወደ አዲስ የእድል በሮች የመቀየር ብቃትን ማሳደግ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በወንድማማችነትና እህትማማችነት እንዲሁም በአብሮነትና በጋራ የጀመርነውን የአገር ግንባታ ስራዎችንም በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ የተገኙት የጸጥታ አካላት በሰጡት አስተያየት፤ በአባቶቻችን መሥዋዕትነትና ጀግንነት ተከብራ የቆየችውን ኢትዮጵያን የማጽናት ተግባርን አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
ሰላምን በማጽናት የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ እንደሚያበረክቱ ተናግረዋል።