ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ማስጠበቅ ሠራዊቱ በጽናት የሚፈጽመው ተግባር ነው

ሃዋሳ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ) ፦ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ማስጠበቅና ልማቷን ማስቀጠል ሠራዊቱ በጽናት የሚፈጽመው ተግባር መሆኑን የደቡብ እዝ መከላከያ ሠራዊት አባላት ገለጹ፡፡

የጳጉሜን ቀናት የኢትዮጵያን ማንሰራራት እና የተገኙ ሁለንተናዊ ስኬቶችን በሚያሳይ መልኩ እየተከበሩ ሲሆን ጳጉሜ-3 “የጽናት ቀን” ሆኖ ሃገርን ለማጽናት ዋጋ የከፈሉ ጀግኖችን በማሰብ እየተከበረ ይገኛል።

ቀኑን አስመለክቶ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የደቡብ እዝ መከላከያ ሠራዊት አባላት እንደገለጹት የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት በማስጠበቅ ልማቷን ማስቀጠል ሠራዊቱ በጽናት የሚፈጽመው ተግባር ነው፡፡

የደቡብ እዝ የኋላ ደጀን አስተባባሪ ኮሎኔል ተሻለ ኡማ እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ በየዘመናቱ የገጠሟትን ፈተናዎች የተሻገረችው ሃገር ወዳድ የሆኑ ጀግኖች በከፈሉት መስዋዕትነትና ባሳዩት ጽናት ነው፡፡

ዛሬም የሠራዊቱ አባላት ከውጭና ከውስጥ ሃገርን ለማፍረስ የሚጥሩ ጸረ ሰላም ሃይሎችን በጽናት በመታገል የሃገርን ክብርና ሉአላዊነት የማስጠበቅና ልማቷን የማስቀጠል ሃላፊነቱን በብቃት እየተወጡ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድም ለሃገር ሲባል የተከፈለውን መስዋዕትነት በመረዳት ለሃገር እድገትና ልማት በጽናት መስራት እንዳለበትና ጸረ ሰላም ሃይሎችን በጋራ መታገል እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የጽናት ቀን ሲታሰብም ሃገርን፣ አንድነትና ሰላምን ማስቀደም እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

በእዙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሃላፊ ተወካይ ሌተናል ኮሎኔል ታመነች አሰፋ በበኩላቸው የሠራዊቱ አባላት ሃገርን ለማጽናት የሚከፍሉት መስዋዕትነት ከሀገር ፍቅር ስሜት የሚመነጭና የጽናት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

የሃገርን ሉአላዊነትና ዳር ድንበር ለማስከበር በየጊዜያቱ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በጽናት ማለፍ ጠንካራ ሃገር እንድትኖረን አድርጎናል ያሉት ሌተናል ኮሎኔሏ፣ የአሁኑ ትውልድም ይህንን ማስቀጠል አለበት ብለዋል፡፡

ዛሬም የኢትዮጵያዊያን ጽናት ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ጨምሮ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማሳካት ጭምር እየተገለጸ መሆኑን ጠቁመው፣ የሀገርን እድገት ለማደናቀፍ የሚጥሩ ጸረ ሰላም ሃይሎችን በጋራ መታገል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ሀገር ሉአላዊነቷ ተከብሮ በጽናት የቆመችው ዘመናዊ መሳሪያ ሳይታጠቁ በአንድነት በታገሉ ጀግኖች አባቶች በከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑን የተናገሩ ደግሞ የእዙ የሠራዊት ስነልቦና ግንባታ ሃላፊ ኮሎኔል ወንድሰን አስፋው ናቸው፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትም ከጀግኖች አባቶች የተረከቧትን ኢትዮጵያ ከነሙሉ ክብሯ ለቀጣይ ትውልድ ለማቆየት ያለብንን ትልቅ ሃገራዊ ሃላፊነት በጀግንነት ለመወጣት በጽናት እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

የሠራዊት ጽናት የሚለካው በሀገር ፍቅር ስሜት መሆኑን የገለጹት ኮሌኔሉ፣ ሉአላዊነቷን ለማስከበርና ዳር ድንበሯን ለማስጠበቅ የሚከፍለው መስዋዕትነት ዛሬም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ዛሬ የኢትዮጵያዊያን ጽናትም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስቀጠልና የሃገር ባንዳዎችን በመታገል መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

የሠራዊቱ አባላት ትውልዱ በተሰማራበት የሥራ መስክ ውጤታማ በመሆን የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ማረጋገጥና በሃገር ክብርና ሉአላዊነት የማይደራደር መሆን እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም