ለዘመን መለወጫ በዓል ከተዘጋጀው ባዛር አስፈላጊ ምርቶችን በአንድ ቦታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘን ነው - ሸማቾች - ኢዜአ አማርኛ
ለዘመን መለወጫ በዓል ከተዘጋጀው ባዛር አስፈላጊ ምርቶችን በአንድ ቦታ እና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኘን ነው - ሸማቾች
ጭሮ፣ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡-በጭሮ ከተማ ለዘመን መለወጫ በዓል በተዘጋጀው ባዛር ለአዲሱ ዓመት የሚያስፈልጓቸውን ምርቶች በአንድ ቦታና በተመጣጣኝ ዋጋ እያገኙ መሆናቸውን ሸማቾች ገለጹ።
በዓላትን ምክንያት በማድረግ የሚዘጋጁ የንግድ ባዛሮችና ኤግዚቢሽኖች በኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጠረውን የኢኮኖሚ ጫና ለመቀነስ እና የገበያ መረጋጋትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና አላቸው።
በተለይም ከአምራቾች፣ ከኢንዱስትሪዎችና ከአቅራቢዎች ምርቶችን በቀጥታ ለሸማቹ ማቅረብ መቻሉ አላስፈላጊ ደላሎችን በማስቀረት የዋጋ ንረትን ለመግታት ያስችላል።
በጭሮ ከተማ የተዘጋጀው የበዓል ባዛርም ኅብረተሰቡ ለአዲሱ ዓመት የሚያስፈልጉትን የግብርና እና የኢንዱስትሪ ፍጆታዎችን በአንድ ማዕከል እና ከወትሮው ገበያ በተሻለ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ የታለመ ነው።
ይህም የሸማቹን የመግዛት አቅም ከማሳደጉም በላይ፣ የበዓሉ ገበያ ሰላማዊና የተረጋጋ እንዲሆን የሚያደርግ የልማትና የንግድ ትስስር እንቅስቃሴ አካል ነው።
በባዛሩ ከተገኙት ሸማቾች መካከል አንዳንዶቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በተለይም በበዓላት ወቅት በበዓል ገበያ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚታይባቸው ምርቶች ባዛሩ ላይ በተመጣጣኝና አነስተኛ ዋጋ እንደቀረቡላቸው ገልጸዋል።
ከሸማቾቹ መካከል አቶ ሽመልስ ብሩ፤ በመደበኛው ገበያ እስከ 900 ብር የሚሸጥ መካከለኛ ዶሮ በባዛሩ በ600 ብር መግዛታቸውን ገልጸው፣ እንዲህ ያሉ ባዛሮች በበዓላት ወቅት መዘጋጀታቸው ለሸማቹ ትልቅ እፎይታ እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
እንደ ሽንኩርት፣ ዶሮ እና እንቁላል ያሉ የበዓል ምርቶች በብዛትና በተመጣጣኝ ዋጋ መቅረባቸው በዓሉን በተሟላ እና በድምቀት ለማክበር የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የበዓል ወቅቱን አስመልከተው አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ መስፍን ሀይሌ፣ በአነስተኛ ዋጋ የቀረበው ምርት በዓሉን በድምቀት ለማክበር እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ደጀኔ ጋሪ በበኩላቸው፣ በመደበኛው ገበያ እስከ 1 ሺህ 100 ብር ይሸጥ የነበረውን የሦስት ሊትር ዘይት በ950 ብር መግዛታቸውን ተናግረዋል።
ይህም ለበዓሉ የሚያስፈልጉ ሌሎች ምርቶችን ለመግዛት ተጨማሪ አቅም እንደሆናቸው ገልጸዋል።
ሸማቾቹ እንደሚሉት፣ በተለይም ዘይት በመደበኛው ገበያ ከሚገኘው ዋጋ በ170 ብር ቅናሽ የቀረበ ሲሆን፣ እንቁላልም በአንዱ የአምስት ብር ቅናሽ ተደርጎበታል።
የጭሮ ከተማ ንግድ፣ ሥራ ፈጠራና ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተወካይ አቶ አደም ዩሱፍ፣ ህብረተሰቡ የሕብረት ሥራ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ከትናንት ጀምሮ እስከ ጳጉሜ 5 የሚቆይ ባዛር መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በባዛሩ ከጭሮ ከተማና ከጭሮ ወረዳ የተወጣጡ 14 አምራቾችና አከፋፋዮች እንዲሁም አንድ የሕብረት ሥራ ዩኒየን ምርቶቻቸውን ለሸማቾች እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።
በባዛሩ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ እንቁላልና ዶሮን ጨምሮ ሌሎች ለዘመን መለወጫ በዓል የሚያስፈልጉ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋና በበቂ መጠን መቅረባቸውንም አቶ አደም ገልጸዋል።