ሰላምን በማጽናት የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የተጀመሩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ እንሰራለን - ኢዜአ አማርኛ
ሰላምን በማጽናት የተመዘገቡ ስኬቶችን እና የተጀመሩ ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ እንሰራለን
ገንዳ ውኃ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የተገኘውን ሰላም በማጽናት የተጀመሩ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ የሀገር መከላከያ ሰራዊትና የፖሊስ አመራር አባላት ገለጹ።
የጳጉሜን ወር ሶስተኛ ቀን የሆነው "የፅናት ቀን" በፌደራልና በክልል የፀጥታ አባላት በተለያዩ ሀገራዊና ህዝባዊ ሁነቶች በድምቀት ተከብሮ ውሏል።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት 50ኛ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጎሽማቸው ስዩም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የፀጥታ ኃይሉ የሀገርን ሰላምና ሉዓላዊነት በማስከበር ለልማት ስራዎች መሳካት ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል።
በፅናት የተመዘገቡ ታላላቅ ስኬቶችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ ጀግኖች አባቶች የወደቁለትን ዓላማ ዳር ለማድረስ ሰራዊቱ ዛሬም ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ምስጋናው ካሴ በበኩላቸው፤ የውስጥ አንድነትን አጠናክሮ ማስቀጠል የሰላምና የልማት መሰረት መሆኑን ገልጸዋል።
ሀገር የሚፀናው የፀጥታ ኃይሉንና ህዝብን ባቀናጀና በተጠናከረ ክንድ በመሆኑ መላው ህዝብ ለሰላም መጽናት መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የተጀመሩ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ያለአንዳች የፀጥታ ስጋት ፍጻሜ እንዲያገኙ አካባቢን በንቅናቄ የመጠበቁ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ተወካይና የሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረሰ አዱኛ የፀጥታ ኃይሉ ለህዝብና ለሀገር ሰላም የሚያደርገውን ተጋድሎ በማድነቅ ነው የገለጹት።
የፀጥታ ኃይሉ ህዝባዊ ወገንተኝነትን ተላብሶ የተጣለበትን አደራ በብቃት መወጣት እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።
የዞኑ አስተዳደርና ህዝብም ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማፋጠን በሚደረገው ጥረት አጋርነታቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል።