የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ባከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት የጽናት ምሳሌ ሆነዋል - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ባከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት የጽናት ምሳሌ ሆነዋል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ባከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት የጽናት ምሳሌ ሆነዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ ገለጹ።
ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን ጳጉሜን 3 የጽናት ቀንን የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበሩ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል መላኩ ፋንታ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ባከናወኗቸው ውጤታማ ተግባራት የጽናት ምሳሌ ሆነዋል።
ዕለቱ ኢትዮጵያ ወደ ማንሠራራት ምዕራፍ መሸጋገሯን የሚያበስር መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (INSA) እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሕዝብና የሀገርን ጥቅም ከማስከበር አንጻር ውጤታማ ሥራዎችን ሠርተዋል ብለዋል።
የሀገር መከታና የጽናት ተምሳሌት በመሆን እንዲሁም በየዘርፋቸው ውጤታማ ሥራዎችን በማከናወን የላቀ ሀገራዊ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ጠቁመዋል።
ቀኑ በቀጣይም ለላቀ ውጤት ቃል የሚገባበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም ገልጸዋል።