ሠራዊቱ ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ከማጽናት ባሻገር የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅና ወታደራዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ - ኢዜአ አማርኛ
ሠራዊቱ ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ከማጽናት ባሻገር የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅና ወታደራዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል - ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ ከማጽናት ባሻገር የቀጣናውን ሰላም በማስጠበቅና ወታደራዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊ ሉዓላዊነትንና የሕዝቦችን ደኅንነት አስተማማኝ በሆነ መንገድ በማጽናት ሂደት ውስጥ የላቀ ሚና እየተወጣ ይገኛል።
ሠራዊቱ የሚቃጡ የተለያዩ የደኅንነት ሥጋቶችን በብቃት በመመከት፣ ሀገርን በጠንካራ መሠረት ላይ የመገንባት ተልዕኮውን በትጋትና በስኬት በማከናወን ላይ ነው።
ከሀገር ተሻግሮም የቀጣናውንና የጎረቤት ሀገራትን ሰላም በማጽናት ታሪካዊ ኃላፊነቱንና አስተዋጽኦውን ሲያበረክት ቆይቷል።
ቀደም ሲል በኮሪያ፣ በኮንጎ፣ በሱዳንና በላይቤሪያና በሌሎችም የተሰጡትን ዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች በብቃት የተወጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፤ አሁንም ቢሆን በደቡብ ሱዳንና በሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎችን በላቀ ዝግጁነትና ብቃት በመፈጸም የቀጣናውን ሰላም በማረጋገጥ ላይ ይገኛል።
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከል ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል አዳምነህ መንግሥቴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ በውስጥና በውጭ የሚቃጡ የደኅንነት ሥጋቶችን የመከላከልና የሀገርን ሰላም የማጽናት ከፍተኛ አቅሙን አረጋግጧል።
ሠራዊቱ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሰማራት የሀገራቱን ሰላም በብቃት በማጽናት አስተማማኝ የሰላም ዘብ መሆኑን በተግባር ማስመስከሩንም ተናግረዋል።
የመከላከያ ሰላም ማስከበር ማዕከልም ይህንን ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት የሚችሉ ዝግጁ የሠራዊት ክፍሎችን የመፍጠር ሥራውን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ዋነኛ ተልዕኮ ሕዝብና ሀገርን መጠበቅ መሆኑን ያመለከቱት ሜጀር ጄኔራሉ፤ ሠራዊቱ ይህንን ሀገራዊ ተልዕኮ በላቀ ስኬት ማከናወኑን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።