ቀጥታ፡

ጽናት እና ኢትዮጵያዊነት አይነጣጠሉም

ጅማ፤ ጳጉሜን 03/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ያሳለፏቸው ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችና ሀገርን የማዳን ጽናት ከማንነታቸው ጋር ፈጽሞ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አባላት አስታወቁ።

ጳጉሜ 3 የፅናት ቀን በጅማ ከተማ በተለያዩ ስነስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል።

በዚህ መርሐግብር በሀገር መከላከያ ሰራዊት የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ አመራሮችና አባላት የተገኙ ሲሆን፤ የጅማ ከተማ ከንቲባ፣ የፀጥታ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችም የታደሙበት ነበር።


 

የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የስነ ልቦና ግንባታ ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል አርጋው ለገሠ ጽናትና ኢትዮጵያዊነት የማይነጣጠሉ በመሆናቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥንካሬና በድል አድራጊነት ዛሬም ለሀገሩ መቆሙን ገልጸዋል።

ጽናት ጥንካሬን መላበስን፣ በችግር ጊዜ አለመሸነፍን እና ለተሰጠ አደራ በቁርጠኝነት መቆምን እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለሀገሩና ለሚወደው ሕዝብ ዋጋ የሚከፍል፣ የሕዝቡን ሰላምና ደህንነት በቁርጠኝነት የሚጠብቅ የሕዝብ አገልጋይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሠራዊት በጽናት የቆመ፣ ሀገርንና ሕዝብን ከሚያሰጋ ጠላት ጋር በቁርጠኝነት የሚፋለም ጠንካራ ሠራዊት ነው ሲሉም ሌተናል ኮሎኔል አርጋው ገልጸዋል።


 

ኢትዮጵያዊነት የማይበገር ጽናት ነው ሲሉ የገለጹት ደግሞ የዳሎል ማዕከላዊ ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሻምበል ፍፁም ብስራት እና ሻምበል እንግዳው ታደሰ ናቸው።

አባቶቻችን በደማቸው ጠብቀው ያስረከቡንን ሀገር የሀገር መከላከያ ሠራዊት በደሙ ጠብቆ ያስቀጥላል ሲሉም አባላቱ አክለው ተናግረዋል።

በተመሳሳይ የዕዙ አባላት የሆኑት ሲኒየር ዋራንት ኦፊሰር አህመድ አብደላ እና መቶ አለቃ ዮሴፍ ጉርቢያው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዛሬም በብቁ ቴክኖሎጂ ታግዞ በጠንካራ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፤ የዚህ ሠራዊት አባል መሆን እጅግ እንደሚያኮራ ተናግረዋል።

ጽናት ማለት ለሀገርና ለሕዝብ በታማኝነት መቆም እና መስዋዕት መሆን መሆኑን የዕዙ አባላት ገልጸው፤ ለሀገር ሕይወትን መክፈል ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ታላቅ ኩራት መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ በቁርጠኝነት መስራታችንን እንቀጥላለን ሲሉም የዕዙ አባላት ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።

በክብረ በዓሉ ላይ የተገኙት የጅማ ከተማ ከንቲባ ጠሃ ቀመር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት በፈተና ውስጥ ብታልፍም በልጆቿ መስዋዕትነት ጸንታ ዛሬም በድል አድራጊነት መቆሟን ገልጸዋል።

ከንቲባ ጠሃ አያይዘውም የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዛሬም ዋጋ በመክፈል ሀገርና ሕዝብን በመጠበቅ ሀገርን በማሻገር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ዛሬም አንድነታችንን በማጠናከር በየአካባቢያችን ሁሉም ዜጎች በእኩልነት የሚኖሩባትን ሀገር አጽንተን ልናስቀጥል ይገባል ሲሉም አቶ ጠሃ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም