ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች - አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት የጽናት ቀንን “ጽናት ለኢትዮጵያ ማንሠራራት” በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እያከበሩ ይገኛሉ።


 

በመድረኩ የመከላከያ ሠራዊት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሥራ እንቅስቃሴዎች ተዘክረዋል።

የቀኑ ዋነኛ ዓላማ ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ማንሠራራት በየዘርፉ እያከናወኑት ላለው ሥራ እውቅና መስጠትና ቀጣይ ተልዕኮዎችን በላቀ ደረጃ ማስቀጠል መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያን ብልፅግና እውን ለማድረግ በሚደረገው ሀገራዊ ርብርብ የተቋማቱ ሚና፣ እየተገኙ ያሉ ውጤቶችና መልካም ተሞክሮዎች እንደሚዳሰሱ ተመላክቷል።


 

ተቋማቱ በሀገር ግንባታ ሂደት፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር፣ ሰላምን በማጽናትና የሀገርን ሉዓላዊነት በማስከበር ዙሪያ ያከናወኗቸው አኩሪ ተግባራትም ይዘከራሉ።

በዚሁ መርሃ ግብር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዲሁም የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችና አባላት ተገኝተዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የተለያዩ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ አኩሪ ድሎችን እያስመዘገበች ትገኛለች።

ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መካሄዱን ያወሱት አፈ-ጉባኤው፤ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታና የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ በውጤት መጠናቀቃቸው የኢትዮጵያውያን የጽናት ማሳያዎች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

አክለውም የባሕር በር ጥያቄን ለመመለስ የተጀመረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሌላው የኢትዮጵያን የጽናት ጉዞ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ሆኖም ይህ ሀገራዊ የዕድገትና የብልፅግና ጉዞ እንዳይሳካ የሚሰሩ የውስጥና የውጭ አካላት መኖራቸውን ጠቁመው፤ መሰል እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የማይናወጥ ብሔራዊ አንድነት፣ ጠንካራ ሀገራዊ መግባባትና ትስስር መፍጠር ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።

ወጣቱ ትውልድም የቀደሙ አባቶች መስዋዕትነት ከፍለው ያቆዩዋትን ሀገር በጽናት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የጸጥታና ደኅንነት ተቋማት ሀገርን በማጽናት ረገድ እየተጫወቱ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም