ቀጥታ፡

ለዘመን መለወጫ የእርድ እንስሳት እና የበዓል ፍጆታ ቁሶች በበቂ ሁኔታ ቀርበዋል

ጉደር፤ ጳጉሜን 3/2018(ኢዜአ)፡- ለዘመን መለወጫ የበዓል ገበያ የእርድ እንስሳት እና የተለያዩ የበዓል ፍጆታ ምርቶች አቅርቦት በቂ መሆኑን በምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ ነጋዴዎችና ሸማቾች አስታወቁ።

የዘመን መለወጫ በዓል ሲቃረብ በየአካባቢው የሚከፈቱ የበዓል ገበያዎች ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚታይባቸው ናቸው። 


 

በተለይም የገበያውን ፍላጎትና አቅርቦት ለማጣጣም ከተለያዩ ክልሎች ወደ ዋና ዋና ከተሞች የሚገቡ የእርድ እንስሳት እንዲሁም የመሠረታዊ ምግብ ነክ ቁሶች ስርጭት የተሻለ እንዲሆን በሁሉም አካላት ጥረት ተደርጓል።

የአቅርቦቱ ማደግ ደግሞ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪን በመግታት ህብረተሰቡ እንደየምርጫውና እንደአቅሙ ገበያ ወጥቶ እንዲሸምት መንገድ አመቻችቷል።


 

ኢዜአ ያነጋገራቸው የጉደር ከተማ ነጋዴዎችና ሸማቾች፤ ለአዲሱ ዓመት በዓል የሚሆኑ የእርድ እንስሳት እና የተለያዩ የፍጆታ ምርቶች በበቂ ሁኔታ ለገበያ በመቅረባቸው፣ ህብረተሰቡ እንደየአቅሙ እየተገበያየ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በከተማው የቁም እንስሳት ገበያ ከተገኙት ሸማቾች መካከል አቶ ንጉሴ ከፈኒ፤ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ አቅርቦትና የተረጋጋ ግብይት መኖሩን ገልጸዋል።

የዘንድሮው የአዲሱ ዓመት የበዓል ገበያ ዋጋ ተመጣጣኝ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንደየአቅሙ እየተገበያየ እንደሚገኝ በመጥቀስ፤ የምርቶች አቅርቦትም በስፋት እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ነጋዴ አቶ አሰፋ ሽብሩ በበኩላቸው፤ የእርድ እንስሳት አቅርቦቱ በቂ ቢሆንም መጠነኛ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን ጠቁመው፣ በገበያው ከፍተኛው የሰባ በሬ እስከ 150 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዓሉ የደስታና የመረዳዳት እንዲሆንም ያላቸው ከሌላቸው ጋር በመቋደስ ማሳለፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የበዓሉ ገበያ የተረጋጋ መሆኑንና የአትክልትና ፍራፍሬ አቅርቦት በብዛትና በጥራት መኖሩን የገለፁት ወይዘሮ አስካለች አለሙ ናቸው፡፡ 


 

በተጨማሪም አላስፈላጊ የዋጋ ንረት እንዳይኖር የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቁጥጥር እያደረጉ መሆኑን ጠቁመው፣ እስካሁን ጥሩ የግብይት እንቅስቃሴ መኖሩን ገልጸዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ንግድ ጽሕፈት ቤት ተወካይ አቶ ተሰማ ኩምሳ፤ ለበዓሉ ከዞን እስከ ቀበሌ የሚደርስ ኮሚቴ በማደራጀት ህብረተሰቡ የበዓል ፍጆታ ምርቶችንና የእርድ እንስሳትን ያለ አቅርቦት እጥረት እንዲያገኝ መደረጉን ገልጸዋል።

በግብይት ሂደቱ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች ከተስተዋሉ ህብረተሰቡ ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ያነሱት ተወካዩ፣ በሁሉም አካባቢዎች ጥብቅ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አምራችና ሸማች በቀጥታ የሚገናኙባቸው የገበያ ማዕከላት በመቋቋማቸው ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲገበያይ እድል መፈጠሩን ያነሱት ተወካዩ፣ ለአዲሱ ዓመት በዓሉ የዶሮ፣ የበግና የፍየል አቅርቦት በስፋት መኖሩን ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም