ቀጥታ፡

ቀደምት አባቶች ያስረከቡንን ሀገር ክብሯን ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ በጽናት እንቆማለን-የሰራዊት አባላት

ሀረር፤ ጳጉሜን 3/2018 (ኢዜአ)፡- ቀደምት አባቶች በመስዋእትነት ያስረከቡንን ሀገር  ክብሯን ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ በጽናት እንቆማለን ሲሉ በሀገር መከላከያ ሰራዊት  የምስራቅ እዝ አባላት  አስታወቁ።

ጳጉሜን 3 የጽናት ቀን  በሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትም እለቱን በማስመልከት ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

የሰራዊት አባላቱም ጽናት ሀገርና ህዝብን ለማሻገር የሚከፈል ዋጋ መሆኑን በመግለጽ የጥንት አባቶች  በመስዋእትነት ያስረከቡንን ሀገር  ክብሯን ጠብቀን ለትውልድ ለማስተላለፍ በጽናት እንቆማለን ብለዋል።

ከሰራዊቱ አባላት መካከል ሌተናል ኮሎኔል ፈይሳ በዳዳ እንደገለጹት ቀደምት አባቶቻችን በውጪ ወራሪ ሀይልና በውስጥ ባንዳ ሳይበገሩ በከፈሉት መስዋእትነት ዳር ድንበሯና የህዝቧ አንድነት የተከበረባት ሀገርን አስረክበውናል   ።

ይህ አይበገሬነት “የጽናት ተምሳሌት ነው” ያሉት ሌተናል ኮሎኔል ፈይሳ የመከላከያ ሰራዊት አሁን ላይ የሀገሩን ዳር ድንበር የማስከበር ሀላፊነቱን በጽናት እየተወጣ መሆኑን አስታውቀዋል ።

“ያለችን ሀገር አንድ ኢትዮጵያ ነች” ያሉት ሌተናል ኮሎኔል ፈይሳ ለውጪና የውስጥ ጠላት ሳንበገር  በታሪክ ቅብብሎሽ የተረከብናትን ሀገር በመጠበቅና በማጽናት  ለመጪው ትውልድ እናስተላልፋለን ብለዋል።

በሀገሪቱ የጽናት ቀን መከበሩም በተለይ ለመከላከያ ሰራዊቱ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑንም ገልጿል።


 

የሰራዊት አባላት  የጥንት አባቶች በከፈሉት መስዋእትነት ዳር ድንበሯ ተከብሮ የቆየችን ሀገር ከጠላት በመጠበቅ  በጽናት የማስቀጠል ሀላፊነታችንን የበለጠ እንወጣለን ያሉት ደግሞ ጁኒየር ዋረንት ኦፊሰር አብረሃም ኢሳያስ ናቸው።

 በዚህም ሰራዊቱ በተሰለፈበት  ሁሉ ግዳጁን በጀግንነት እየተወጣና  ድል እየተቀዳጀ ይገኛል  ሲሉ ተናግረዋል ።

በጀግኖች አባቶች መስዋዕትነት ጸንታ  የቆየችን ሀገር በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሀላፊነታቸውን በበለጠ እንደሚወጡ አስታውቀዋል ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም