በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ 978 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ 978 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል
ጂንካ፥ ጳጉሜ 2/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት አመት በቱሪዝም ዘርፍ 978 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይኒቱ መልኩ በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት አመት ከቱሪዝም ዘርፍ 500 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰዋል።
ይሁን እንጂ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ከእቅድ በላይ 978 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ተናግረዋል።
በክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ በስፋት በመሰራቱና የጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ለገቢው ማደግ በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የሙሩሌ የቁጥጥር አደን ቦታ፣ የማጎና የማዜ ብሔራዊ ፓርኮች የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር ዓለም አቀፍ መካነ ቅርስ በክልሉ ከሚገኙ የቱሪስት መዳረሻዎች ዋነኞቹ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
የአርባምንጭ አዞ እርባታ፣ የባንባላ ተንጠልጣይ ድልድይ፣ የዳሞ ተራራና የጌዴኦ ትክል ድንጋዮች መካነ ቅርስም በስፋት እየተጎበኙ ያሉ የመስህብ ስፍራዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በበጀት አመቱ 13 ሚሊዮን የሀገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች የመስህብ ስፍራዎቹን መጎብኘታቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ የጎብኚዎች ቁጥር መጨመርም ለቢዝነስ ቱሪዝም መነቃቃት እና ለስራ እድል ፈጠራ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውቀዋል።
የማጎ ብሔራዊ ፓርክ አስተዳዳሪ አቶ ኤርቦር ሌለ በበኩላቸው ፓርኩን ለመመልከት ወደ ስፍራው የሚመጡ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
ፓርኩ ከ80 በላይ አጥቢ፣ ከ250 በላይ የአዕዋፍና 14 ዓይነት የዓሣ ዝርያዎችን የያዘ መሆኑን አመልክተዋል።