ቀጥታ፡

በደቡብ ወሎ ዞን በተለያዩ ዘርፎች የተመዘገቡ ውጤቶች የኢትዮጵያ የማንሰራራት ተምሳሌት ናቸው

ቃሉ፤ ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ)፡-በደቡብ ወሎ ዞን  በኢንቨሰትመንት፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በፍራፍሬ እና የኮሪደር ልማት መስኮች የተመዘገቡ አበረታች ውጤቶች የኢትዮጵያ ማንሰራራት በተጨባጭ የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የዞኑ መስተዳድር ገለፀ።

በዞኑ የማንሰራራት ቀን ምክንያት በማድረግ በቃሉ ወረዳ እና ሀርቡ ከተማ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ጉብኝት ተካሂዷል።

በጉብኝቱ የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንድሪስ ይማም እንደገለጹ፣ በዞኑ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ አበረታች ውጤት ተመዝግቧል።

በተለይ በኢንቨሰትመንት፣ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ የፍራፍሬ እና ኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማ ልማት፣ በንጹህ መጠጥ ውሃና በሌሎችም የተመዘገቡ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የኢትዮጵያ እያንሰራራች መሆኑን ያመላክታሉ ነው ያሉት።

በከተሞቹ የጠጠር ማምረቻ፣ የኮሪደር ልማት፣ ተንጠልጣይ ድልድይና ሌሎችም ልማቶች ተስፋ ሰጪ እና የኢትዮጵያን ማንሰራራት ለማስቀጠል  የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የዞኑ ማዕድን ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ አህመድ አበባው በበኩላቸው፣ በዞኑ ከሚገኘው በርካታ የማዕድን ሀብት በአግባቡ እና በዘላቂነት  ተጠቃሚ ለመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማው በተሰሩ ሰፋፊ ልማቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ የሀርቡ ከተማ ነዋሪ ሸህ ሰይድ ሀሰን እና ሹምነሽ ኢብራሂም  ናቸው።

በተለይ የኮሪደር ልማቱ የከተማውን ውበት በማሳመር ለነዋሪዎች ምቹ የሥራ አከባቢን የፈጠረ ሲሆን  በወረዳው እየተገነቡ ባሉ ሰው ተኮር ፕሮጀክቶች ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከዚህ ውስጥም በተገነቡ የንፁህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ችግራቸው በመቀረፉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በጉብኝቱ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም