ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ማንሰራራትን የሚያፀኑ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች አከናውናለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ማንሰራራትን የሚያፀኑ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች አከናውናለች
አዲስ አበባ ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራዊ ማንሰራራትን የሚያፀኑ ሜጋ የልማት ፕሮጀክቶች ማከናወኗን የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ገለጸ።
ዛሬ የጳጉሜን 2 የ"ማንሰራራት ቀን"ን ምክንያት በማድረግ የስድስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ዐበይት የልማት እንቅስቃሴዎች የሚያሳይ የፎቶ አውደ ርዕይ ሲከፈት የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍራኦል ጣፋ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያን ማንሰራራት የሚያፀኑ የልማት ሥራዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ነው።
መንግስት በሁሉም ተቋማት የሕዝቡን ጥያቄዎች በመመለስ የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያለመልሙ ትልልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችና ኢኒሼቲቮች ቀርፆ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል።
የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎቱን የሚያዘምኑ በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች መከናወናቸውን ገልጸው፤ የፎቶ አውደ ርዕዩ ተቋማት በትብብርና በቅንጅት የፈጠሯቸውን ሀገራዊ የልማት ውጤቶችና አቅሞችን በግልጽ ያሳያል ብለዋል።
በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አመለወርቅ ህዝቅኤል፤ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የነዳጅ ወጪና የአየር ንብረት ለውጥን ታሳቢ ያደረገ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ግዢ እንደሚፈጸም ገልጸዋል።
የሞጆ ደረቅ ወደብ የአረንጓዴ ሎጂስቲክስ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ ሀገራዊ የሎጅስቲክስ ምህዳሩን ያዘምነዋል ብለዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ኢትዮጵያ በዴቻ፤ መንግሥት አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ ከተሞች ገቢራዊ ያደረገው የኮሪደር ልማት የነዋሪዎችን የአኗኗር ዘይቤ መቀየሩን ገልጸዋል።
ከዚህም ባለፈ የመንግሥትና የግሉን አጋርነት በማጠናከር እስከ 10 ዓመታት ይወስዱ የነበሩ የቤት ግንባታዎችን በወራት ውስጥ በማጠናቀቅ ለከተሞች ዝማኔ ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል።
በቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ብዙዓለም ጌቱ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለቱሪዝም ልማት ፖሊሲ በመቅረጽ ዘርፉ የሚያመነጨውን ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
እንደ ጅማ አባ ጅፋርና የጎንደር ፋሲለደስ ያሉ ታሪካዊ ቅርሶች ከመጠገን ባለፈ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገርና ገበታ ለትውልድ የተገነቡ የቱሪዝም ሀብቶች ሀገሪቱን የቱሪስት መዳረሻ አድርጓታል ብለዋል።