ወጣቶች በሀገር፣ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ወጣቶች በሀገር፣ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ):-ወጣቶች በሀገር፣ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያደርጉትን ተሳትፎ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ገለጸ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ለአንድ ወር ሲያካሂድ የቆየው የሁለተኛ ዙር የክረምት ሥልጠና (Summer Camp) ማጠቃለያ ምረቃ መርሃ ግብር አካሂዷል።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር መሐመድ ራፊ አባራያ እንደገለጹት፤ በአፍሪካ ቀንድና በመላው አህጉራችን የሚታዩት ሁነቶች እጅግ ሰፊና እርስ በርስ የተሳሰሩ ታላላቅ ዕድሎችንና መልካም አጋጣሚዎችን የያዙ ናቸው።
እነዚህን ዕድሎች አውጥቶ ለመጠቀምና ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እውን ለማድረግ፤ በጥልቅ ዕውቀት የበለፀጉ አእምሮዎች፣ ገንቢና በጎ ውይይቶች፣ ከፍተኛ ሙያዊ ብቃት እንዲሁም በቁርጠኝነትና በተስፋ የሚሳተፉ አዳዲስ ብሩህ ትውልድ መሪዎች ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።
ሥልጠናው ወጣቶች ልምድ ካካበቱ ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች እንዲማሩ፣ ሐሳብ እንዲለዋወጡና ወቅታዊ ጉዳዮችን እንዲመረምሩ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ሥልጠናው ሠልጣኞቹ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ቀንድና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉትን ሰፊ ዕድሎችና ነባራዊ ሁኔታዎች በጥልቀት እንዲረዱ ያደርጋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም ዕውቀታቸውንና አቅማቸውን በመጠቀም ለሀገሪቱ ልማት፣ ዕድገትና ብልፅግና የጎላና ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ታላቅ መንገድ ይከፍትላቸዋል ብለዋል።
በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለድርሻ አካላት ሥልጠና ዳይሬክተር ጄነራል መላኩ ሙሉዓለም በበኩላቸው፤ ሥልጠናው ዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ያተኮረና 57 ሠልጣኞችን ያካተተ ነው።
ሠልጣኞቹ ከሀገር አቀፍ ደረጃ የተወጣጡና በውጤትና በብቃት ተወዳድረው መመረጣቸውን አክለዋል።
ሠልጠናው በሀገር፣ አፍሪካና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የንድፈ ሐሳብና የተግባር ልምምድ ያካተተ መሆኑን አመልክተው፤ ለአገሪቷ ዲፕሎማሲ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ወጣቶችን ለማፍራት ያስችላል ብለዋል።
ከተመራቂ ወጣቶች መካከል አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት እንደተናገሩት፤ ሥልጠናው በዲፕሎማሲ ዘርፍ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት በማዳበር በዘርፉ የመሥራት ፍላጎታቸውን አሳድጎላቸዋል።
ወጣት ፌኔት ሞቱማ እንዳለችው ሥልጠናው በቀጣይ በዲፕሎማሲ ዘርፍ ለመሰማራት ብቃቷን ያሳደገላት መሆኑን ገልጻለች።
ወጣት ኪሩቤል በእውቀቱ በበኩሉ ስለ ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ፣ ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል።
ወጣት ፍቅርዓለም ብርሃኑ ሥልጠናው በድርድር፣ በፕሮቶኮልና በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ላይ አዳዲስ እይታዎችን ያላበሰውና በሀገሪቱ ዲፕሎማሲ ላይ አሻራውን ለማሳረፍ ተነሳሽነቱን የጨመረለት መሆኑን ገልጿል።
ወጣት ሮዛ ዓለማው በበኩሏ በዲጂታል ዲፕሎማሲ ሀገሯን ለማገልገል መዘጋጀቷን ተናግራለች።