ቀጥታ፡

ሀገርን ያፀና ጠንካራ ሠራዊት የፈጠረ ሪፎርም

መንግሥት ባለፉት ዓመታት ሪፎርም በማድረግ አመርቂ ስኬቶችን ካስመዘገበባቸው ዘርፎች አንዱ የመከላከያ ሴክተር ነው።

የመከላከያ ዘርፉ አወቃቀርና አሠራር መሠረታዊ ለውጥ ማድረጉ አስገዳጅ በመሆኑ ከለውጡ በፊት የነበሩ ተቋማዊ ፈተናዎችን ለመፍታት ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካና የብሔር ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ ለሕገ-መንግሥቱና ለሀገር ብቻ ታማኝ የሆነ ብሔራዊና ሕዝባዊ ባህሪ እንዲኖረው የሚያስችሉ ስራዎች ተከናውነዋል።

ማንኛውንም የውስጥና የውጭ የደኅንነት ሥጋት በአጭር ጊዜ ውስጥ አምክኖ ማስቀረት የሚችል ዘመናዊ ኃይል ከመፍጠር ባለፈ የሠራዊቱን አባላት ዕውቀት በዓለም አቀፍ የጦር ጥበብና በስትራቴጂካዊ አመራር ደረጃ ማበልጸግ ላይ ውጤታማ ስራዎች ተሰርተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ ታሪክ ዋነኛ መሠረቱ ወታደር ነው አይተኬ ህይወቱን ገብሮ ሀገርና ትውልድ ያጸናል፤ ከሠፈርና ከመንደር የተሻገረ የላቀ አላማ እና መስዋዕትነት የያዘ ሠራዊት ሀገርን ይታደጋል ማለታቸው ይታወሳል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየጊዜው የገጠመው ፈተና የተሻለ ደረጃና አቅም ያለው ሆኖ ዳግም እንዲፈጠር አስችሎታል በማለትም የተከናወነውን የለውጥ ስራ መጠቆማቸው አይዘነጋም ።

በዚህም የሀገሪቱን ስልታዊ ጥቅሞች ለማስከበር የባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት፣ የልዩ ዘመቻዎች ዕዝ እና አዳዲስ የውጊያ ድጋፍ አገልግሎቶችም ተዋቅረዋል።

የሪፎርሙ ማሳያ የሆኑት የሆለታ ገነት እና የሐረር ጦር አካዳሚዎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ወደ ቀድሞ ታሪካዊ ክብራቸው ተመልሰው የወታደራዊ ሳይንስ የልህቀት ማዕከላት እንዲሆኑም ተደርገዋል።

በቴክኖሎጂው ዘርፍም ሠራዊቱ በመሬት ላይ ብቻ ሳይሆን በሳይበር እና በዲጂታል መረጃ ላይ በአንድነት የሚሠራ ባለብዙ ዘርፍ ዝግጁነትን ገንብቷል።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ)፣ በመከላከያ ኢንተርፕሪነርሺፕ እና ኢኖቬሽን ማዕከል እንዲሁም በስካይ ዊን (SkyWin) ኩባንያዎች ትብብር ድሮኖችን በአገር ውስጥ የመገጣጠምና የማምረት ታሪካዊ ስኬትም ተመዝግቧል።

አየር ኃይሉም የላቁ ተዋጊ ጄቶችን በመታጠቅ እና እስከ 2030 ድረስ ወደ 5ኛ ትውልድ ተዋጊ አውሮፕላኖች ለመሸጋገር የሚያስችል ስልታዊ እመርታ አሳይቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሪፎርሙን አስመልክቶ በሰጧቸው አስተያየቶች ላይ የተከናወኑት የለውጥ ሥራዎች የሠራዊቱን የመዋጋትና የመመከት አቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሳደግ የሀገርን ድንበር የተሻገረ ስልታዊና ጂኦፖለቲካዊ ሚና እንዲጫወት ማድረጉን ገልጸዋል።

ሰራዊቱ ለአል-ሸባብ እና መሰል ዓለም አቀፍ አሸባሪ ቡድኖች ቀጣናዊ ምላሽ በመስጠት እና ድንበር ተሻጋሪ ሽብርተኝነትን በመግታት ረገድ ግንባር ቀደም ጋሻ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ከፍተኛ ቁጥር ያለውና በሚገባ የሰለጠነ ሰላም አስከባሪ ኃይል በማሰማራት አህጉራዊ ግጭቶችን የመፍታት የዲሲፕሊንና የውጊያ ጥበብ አርአያነቷን አስመስክራለች።

አዲስ የተደራጀው የባሕር ኃይል እና የልዩ ዘመቻዎች ዕዝም በቀይ ባህርና በህንድ ውቅያኖስ ቀጣና የደህንነት ሥጋቶችን ለመከላከልና ለዓለም አቀፍ የባህር ትራንስፖርት ደህንነት ትልቅ አቅም ይፈጥራል።

የዳበረው ወታደራዊ አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነትን በማስገኘቱ በቅርቡ ከአሜሪካ ጋር የነበረውን የደህንነት ግንኙነት ወደ ስትራቴጂካዊ አጋርነት (Strategic Partnership) ማሳደግ ተችሏል።

መከላከያ ሠራዊቱ የሀገርን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ ከማስጠበቅ ባሻገር፣ ከሕዝብ ጋር ባለው ጠንካራ ማኅበራዊ ትስስር አገራዊ ልማትንና በጎ አድራጎታዊ ሥራዎችን በመደገፍ ረገድ ታላቅ አርአያነትን እያሳየ ይገኛል።

የመከላከያ መሃንዲስ ዋና መምሪያን ጨምሮ የተለያዩ የሠራዊቱ ክፍሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የመንገድና የድልድይ ጥገናዎችን፣ የጎርፍ መከላከያ መሠረተ-ልማቶችን እንዲሁም የውኃ ቁፋሮ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ለሕብረተሰቡ የዕለት ተዕለት ሕይወት መሻሻል የላቀ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ከዚህም ባለፈ ሠራዊቱ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በመሥራት፣ የደም ልገሳ መርሃ ግብሮችን በማካሄድ እና በሚሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ እየተወጣ ይገኛል።

በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት የመከላከያ ሠራዊቱን ከሪፎርም ወደ ትራንስፎርሜሽን በማሸጋገር ተቋማዊ ነፃነቱን ያረጋገጠ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀና የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስከብር ኃይል ሆኖ መውጣቱ የጽናት ተምሳሌት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም