ቀጥታ፡

ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ለዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ትኩረት ተሰጥቷል

ደብረ ብርሃን፤ ጳጉሜ 2/2018  (ኢዜአ)፡-የመንግስት ተቋማት  ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ለዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታ ትኩረት መስጠቱን የሰሜን ሸዋ ዞን ሲቪል ሰርቪስና የሰው ሀብት መምሪያ አስታወቀ፡፡

ጳጉሜ 2 «የማንሰራራት ቀን» አዳዲስ ተስፋዎችን በመሰነቅ፣ ያረጁ አሰራሮችን በዘመናዊ አስተሳሰብ በመተካት ለሀገርና ለህዝብ እድገት በቁርጠኝነት የምንነሳሳበት ልዩ ቀን ነው ሲል መምሪያው አመልክቷል።

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ሜሮን አበበ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ የማንሰራራት ቀንን ፋይዳ መነሻ በማድረግ አዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለህዝብ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል።

በተለይም ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ተቋምን በመገንባት ከብልሹ አሰራር የፀዳ የመንግስት አገልግሎት በመስጠት አገራዊ ማንሰራራቱን በዘላቂነት ለማስቀጠል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

አክለውም ዘመኑን የሚመጥን የመንግስት አገልግሎት አስተዳደር ሪፎርም በመዘርጋት ነፃና ገለልተኛ የሲቪል ሰርቪስ ተቋም ለመገንባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሙሉ በሙሉ የዲጂታል ሲቪል ሰርቪስ ግንባታን እውን ለማድረግም የመንግስት ሰራተኞችን ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል።

ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ለሙስና የሚያጋልጡ አሰራሮችን ለመቀነስና ዘመናዊ አሰራርን ለመዘርጋት ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንም አብራርተዋል።

ለዚህም በቡልጋ፣ በአረርቲ እና በሸዋ ሮቢት ከተማ አስተዳደሮች የመሶብ አንድ ማዕከል ግንባታ ስራ በፍጥነት እየተከናወነ እንደሚገኝ ወይዘሮ ሜሮን አስረድተዋል።

የዲጂታል አሰራር ትግበራው በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር ለማንሰራራት የሚደረገውን ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥን እንደሆነም አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም