ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል በክልላዊ እና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መጥቷል

ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፡-በሲዳማ ክልል የትምህርት ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተከናወኑ ሥራዎች በክልላዊና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት መሻሻል ማሳየቱን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የሲዳማ ክልል ምክትል ርዕስ መስተዳድርና የትምህርት ቢሮ ሀላፊ አቶ በየነ በራሳ እንዳሉት በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን   በክልሉ በሁሉም የትምህርት እርከኖች የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ስራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል። 

የትምህርት ማህበረሰቡን በማነቃነቅ ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥራው በተጨማሪ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል መሰራቱን ተናግረዋል።

በዚህም በክልላዊና በሀገር አቀፍ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።

ባለፉት ዓመታት በ6ኛ እና በ8 ክፍል ክልላዊ ፈተና የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ ዝቅተኛ እንደነበር አቶ በየነ አስታውሰው፣ የትምህርት ማህበረሰቡን በማሳተፍ በተደረገ ጥረት በአሁኑ ወቅት የማለፍ ምጣኔው 62 በመቶ ደርሷል ብለዋል።

በአስራ ሁለተኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናም የተማሪዎች የማለፍ ምጣኔ እየተሻሻለ መምጣቱን ተናግረዋል።

የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ርዕሰ መምህርት ጽዮን ታደገ እንዳሉት፣ ተማሪዎች በፈተና ውጤታማ እንዲሆኑ ሙሉ ትኩረታቸውና ለትምህርት እንዲሰጡ ተደርጓል።

በማጠናከሪያ ትምህርት፣ ተከታታይ ሞዴል ፈተናዎችን በመስጠትና የስነ ልቦና ድጋፍ በማድረግ ተማሪዎችን የማብቃት ሥራ መሰራቱን ገልጸው፣ በዚህም ዘንድሮ ትምህርት ቤቱ ያስፈተናቸው የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች በሙሉ ማለፋቸውን ተናግረዋል።

በወላጆቻቸው፣ በመምህራንና በትምህርት ቤቱ በተደረገላቸው ድጋፍ በሀገር አቀፍ ፈተናው ጥሩ ውጤት ማምጣታቸውን  የተናገሩት ተማሪ ቤቴል ሲሳይ እና ተማሪ ልኡል አለማየሁ ናቸው።

ተማሪ ቤቴል ሲሳይ 532፤ ተማሪ ልኡል አለማየሁ ደግሞ 539 ውጤት ያመጡ ሲሆን በሀገር አቀፍ ፈተና ውጤታማ የሚያደርገው ኩረጃ ሳይሆን በቂ ዝግጅት ማድረግ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። 

ተማሪዎቹ በቀጣይ ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ ጊዜያቸውን ሙሉ በሙሉ በትምህርታቸው ላይ በማድረግ ውጤታማ ለመሆን መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም