በሲዳማ ክልል በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን የሚያፋጥኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን የሚያፋጥኑ ናቸው
ሀዋሳ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን የሚያፋጥኑ መሆናቸው ተገለጸ።
በክልሉ ጳጉሜን 2 “የማንሰራራት ቀን”ን አስመልክቶ በግብርና፣ በመንገድ ትራንስፖርት፣ በማዕድንና ኢነርጂ፣ በከተማና መሰረተ ልማት እንዲሁም በኢንዱስትሪና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ላይ የመስክ ምልከታ ተደርጓል።
በተጨማሪም በተመዘገቡ ስኬቶችና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
በፓናል ውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ መንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አስፋው ጎኔሶ እንደተናገሩት፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የህዝብን ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ተጨባጭ ውጤቶች የተመዘገቡባቸው ተግባራት ተከናውነዋል።
ያሉትን ጸጋዎች ወደ ውጤት ለመቀየር የተደረጉ ጥረቶች አዎንታዊ ውጤት ማምጣታቸውን አውስተው፤ ለአብነትም በግብርናው ዘርፍ የገበያውንና የኢንዱስትሪ ፍላጎቶችን መሸፈን የቻሉ ምርቶች መቅረባቸውን ተናግረዋል።
ከግብርናው ባለፈ በመንገድ ልማት፣ በማዕድን ሀብትና በኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም እንዲሁም ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ለበርካቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩሉን ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።
የልማት ስራዎች የማስፈጸም አቅም እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በቀጣይም የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን ለማፋጠን የክልሉ መንግስት በላቀ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በከተሞችና መሰረተ ልማት ዘርፍ እየታዩ ያሉ አመርቂ ውጤቶችን ማጠናከር በልዩ ትኩረት የሚሰራበት መሆኑን ያነሱት አቶ አስፋው፤ በክልሉ የተያዙ ግቦች በተቀናጀ መልኩ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል ።
አደጋዎችንም በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመሩና የተገኙ አበረታች ጥረቶችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን የተገኙ ስኬቶችን ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በልዩ ትኩረት በመስራት ሀገራዊ የማንሰራራት ጉዞን ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክልሉ በኢኮኖሚና ማህበራዊ ዘርፎች እምርታዊ ለውጥ ያስገኙ ስኬቶ መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የግብርናውን አቅም ለመጠቀም የተደረገው ጥረት የነዋሪውን ተጠቃሚነት ያረጋገጠ ሲሆን፤ ለመስኖ እርሻ የተሰጠው ትኩረትና በእንስሳት ሀብት ልማት የተገኙት ስኬቶች አበረታች መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በክልሉ በተለያዩ ዘርፎች ሁለንተናዊ ስኬት እንዲመዘገብ የተደረጉ ጥረቶች ምቹ መደላድል መፍጠራቸውን በመግለጽ፤ በቀጣይም እነዚህ ተግባራት በላቀ ጥረት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የጳጉሜን ቀናትን መከበራቸው ከትናንትናው ስኬት በመማር ለቀጣይ ዓመት መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ከንግግር ባለፈ በተግባር ለመፈጸም ቃላችንን አድሰን የምንነሳበት ነው ብለዋል።