አፍሪካዊቷ የብልፅግና አብሪ ኮኮብ፤ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ታሪካዊ እጥፋት - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካዊቷ የብልፅግና አብሪ ኮኮብ፤ የኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ታሪካዊ እጥፋት
በመደመር መንግሥት እሳቤ የተቃኘው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲገጥማት የነበረውን የኢኮኖሚ ስብራት በማከም አዳዲስ የዕድገትና ብልጽግና ዕድሎችን ፈጥሯል።
ሪፎርሙ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኖችን ከማስተካከል ባለፈ የምርት አቅምን ማሳደግ፣ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት፣ የፋይናንስ ዘርፉን ማዘመንና የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማስፋት የሚያስችል መሠረት ገንብቷል።
በሁለት ምዕራፎች እየተተገበረ ያለው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነባር ችግሮች ወደ ዘላቂና የምርታማነት ዕድገት በማሸጋገር የዘርፎችን የማንሰራራት ጉዞ እያበሰረ ይገኛል።
ይህም ኢትዮጵያ በ2016 ዓ.ም 8 ነጥብ 1 በመቶ፣ በ2017 ዓ.ም 9 ነጥብ 2 በመቶ ተከታታይ ጥቅል ሀገራዊ ዕድገት እንዲያስመዘግብ እንዲሁም በ2018 ዓ.ም 10 ነጥብ 2 በመቶ ዕድገት እንዲጠበቅ አስችሏል።
በዘርፎች ሲታይም በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ግብርና 7 ነጥብ 3 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ 13 በመቶ እና አገልግሎት 7 ነጥብ 5 በመቶ ጥቅል ዕድገት በማስመዝገብ የዘርፎችን ቀጣይነት ያለው ማንሰራራት አመላካች ሆኗል።
በተለይም በሁለት ምዕራፍ በተከፈለ መርሐ ግብር ተግባራዊ የተደረጉ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሮች የዘርፎችን እመርታዊ ውጤት በማላቅ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እያፋጠኑ ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ማጠቃለያ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንዳሉት፤ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ከተጠበቀው በላይ አመርቂ ውጤት አምጥቷል።
የኢትዮጵያ በእመርታ የታጀበው የኢኮኖሚ ማንሰራራት ስኬት በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት ካላቸው ግንባር ቀደም ሀገራት እንዳደረጋት አስታውሰዋል።
ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውም የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን በማከም ከነባሩ የግብርና መር ክፍለ ኢኮኖሚ ወደ ብዝኅ ዘርፍ በማሸጋገር ጥራት ያለው ዕድገት እንድታስመዘግብ እያስቻለ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም የኢኮኖሚ ማንሰራራትን በጽኑ መሠረት በማነጽ በሁሉም ዘርፍ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የዕድገት ሽግግር የሚሳለጥበትን ሁኔታ እንደፈጠረ አብራርተዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ ያሸጋገረ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብር ትግበራ ቁርጠኝነት አስተማማኝና ቀጣይነት ያለው ዕድገት እንዲመዘገብ ያስቻለ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህም አፍሪካዊት የብልጽግና ተምሳሌት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ በበርካታ መመዘኛ ግቡን እየመታ መሆኑን እንደሚያመላክት አብራርተዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በበኩላቸው፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አመርቂ ውጤት ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ለውጤቱም ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ፣ የሞኒተሪ ፖሊሲ፣ የኢንቨስትመንት ሕግ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች አስቻይ ምኅደር መፈጠሩ የዘርፎችን እመርታዊ የዕድገት ጉዞ ለማስፋት አስችሏል ብለዋል።
የኢትዮጵያ አጠቃላይ እመርታዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የማንሰራራት ጉዞም በዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጭምር የተረጋገጠ ሐቅ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢኮኖሚ ምሁር ተወልደ ግርማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ ግብሩ የዋጋ ግሽበትን በማርገብ የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ ማድረጉን ገልጸዋል።
ለአብነትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ውስጥ በብዙ እጥፍ እንደሚልቅ የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና የአሜሪካ ኢንቨስትመንት ባንኮች በጥናታቸው መተንበያቸውን አንስተዋል።
ሌላኛው የኢኮኖሚ ምሁር ደረጀ ደጀኔ፤ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በሀገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የኢኮኖሚ መነቃቃትን የፈጠረ የፖሊሲ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህም የንግድና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰትን በማበረታታት የኢትዮጵያን ዓለም አቀፍ የንግድ ሚዛን የሚያስጠበቅ የምርታማነትና ቀጣይነት ያለው የዕድገት ምኅደር መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸዋል።