ቀጥታ፡

የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት

ካራት፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፡-የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ፎር አፍሪካ የተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በኮንሶ  ዞን  ካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ውስጥ ያስገነባው የሶላር ሃይል ፕሮጀክት ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።


 

የጤና ሚኒስቴር የስነ-ተዋልዶ፣ የቤተሰብ ዕቅድና የወጣቶች ጤና አገልግሎት ቡድን መሪ ሞቱማ በቀለ በመርሃ ግብሩ ላይ  ተገኝተው እንዳሉት፣ በሀገሪቱ የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ በተደረገ ጥረት ለውጥ ተመዝግቧል። 

በካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሶላር ሃይል መገንባቱ በሆስፒታሉ የጤና አገልግሎቱን ውጤታማ በማድረግ የእናቶችና ሕፃናት ሞት ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ይበልጥ ስኬታማ ያደርጋል ብለዋል።

እንደሀገር የእናቶችና ሕጻናትን ሞት ለመቀነስና የጤና አገልግሎቱን ለማጠናከር በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የክልሉ መንግስት ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በቅንጅት ባከናወነው ተግባር የተሻለ የጤና አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ተችሏል።

በእዚህም የእናቶችና የሕጻናትን ሞት መቀነስን ጨምሮ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ነው የገለጹት።


 

በካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተገንብቶ ለምረቃ የበቃው የሶላር ፕሮጀክት ከሀይል አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሲነሳ የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈታና የጤና ልማት ግቦችን ለማሳካት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

የፎር አፍሪካ ካንትሪ ዳይሬክተር ፀደቀ ደሳለኝ በበኩላቸው ድርጅቱ ከመንግስት፣ ከኮንሶ ልማት ማህበር እና ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ከ120 ሺህ ዩሮ በሚበልጥ ወጪ የሶላር ሀይል ፕሮጀክት በካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ለአገልግሎት  ማብቃቱን ተናግረዋል።

የሶላር ፕሮጀክቱ 128 ኪሎ ዋት ሃይል የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን ይህም ሆስፒታሉ ሃይል ሳይቆራረጥበት ለህብረተሰቡ አስተማማኝና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያስችለዋል ብለዋል፡፡ 


 

ካራት የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ የኮንሶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገሌቦ ጎልቶሞ ናቸው።

ዋና አስተዳዳሪው ፎር አፍሪካ እና ሌሎች ባለድርሻዎች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም