በአማራ ክልል የተገነቡ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉን ማንሰራራት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል የተገነቡ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች የክልሉን ማንሰራራት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው
ባህር ዳር፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች ተገንብተው መጠናቀቅ የክልሉን የማንሰራራትና የለውጥ ምዕራፍ በተግባር እንደሚያረጋግጥ ተገለጸ።
ጳጉሜን-2 የማንሰራራት ቀን ተብሎ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎችየተከበረ ሲሆን በባህር ዳር ከተማም ቀኑ በፓናል ውይይትና በፎቶ ግራፍ አውደ ርይዕ ተከብሯል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ አቶ አብደላ ኑሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በተለያዩ የልማት ሥራዎች የተመዘገቡ ውጤቶች የክልሉን የለውጥ ጉዞና ማንሰራራት የሚያረጋግጡ ናቸው።
በተለይም የህዝብን የአገልግሎት አሰጣጥ ለማሳለጥ በሲቪል ሰርቪስ፣ በፀጥታ፣ በፍትህና መሰል ተቋማት የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ተጨባጭ ለውጥ አምጥተዋል ብለዋል።
በከተሞች ልማት፣ በማዕድን ልማት፣ በግብርና፣ በንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በማድረግና ቴክኖሎጂን በማስፋት አዳጊ ስራዎች መከናወናቸውንም አመልክተዋል።
በይቻላል መንፈስ በክልሉ ህዝብን ተጠቃሚ ያደረጉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ማጠናቀቅ የክልሉን የለውጥና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ ማዕድን ልማት ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ በበኩላቸው በማዕድን ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ውጤት የሀገርና የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ ነው።
ዘርፉ ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት መንግስት ለብዘሀ ዘርፍ በሰጠው ትኩረት ማዕድን የኢኮኖሚው አንድ ምሰሶ ሆኖ በትኩረት እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል።
ባለፉት ጊዜያት 50 ማዕድናትን በጥናት የመለየት ሥራ መሰራቱን ገልጸው የክምችት ግመታና የፍለጋ ሥራም እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 357 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ እና 28 ሺህ ኪሎ ግራም ኦፓል ለውጭ ገበያ እንደቀረበና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ3 ሺህ 500 በላይ የውሃ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለፁት ደግሞ የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ጥላሁን ሽመልስ ናቸው።
በ2019 በጀት ዓመትም የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳካት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብር በጀት ተመድቦ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።
በክልሉ የንፁህ መጠጥ ውሃ እና የአማራጭ ሃይል አቅርቦትን በገጠርና በከተማ ተደራሽ የማድረጉ ሥራ ከመቸውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በመድረኩ የክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች አመራሮች እና ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን የልማት ሥራዎችን የሚያስቃኝ የፎቶ አውደ ርዕይም ተካሄዷል።