የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ርዕይ፤ የመደመር መንግሥት የግንባታ ዘርፍ የማንሰራራት ስንቅ - ኢዜአ አማርኛ
የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት ግንባታ ርዕይ፤ የመደመር መንግሥት የግንባታ ዘርፍ የማንሰራራት ስንቅ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጳጉሜ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት የኢትዮጵያን የብልጽግና ፍኖት የሚያበስሩ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረዋል።
የጉባ ብስራቶችም የኢትዮጵያን ኃይል፣ ኢንዱስትሪ፣ አቪዬሽን፣ ማዕድንና ከተማ ልማት ልህቀት በማጎልበት የሀገርን መቻልና መርህ በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው።
የአዲሱ የቢሾፍቱ ሜጋ አየር ማረፊያ፣ የነዳጅ ዘይት ማጣሪያ፣ ሰላማዊ የኒውክሌር ማብላያ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ፋብሪካ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ እና የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ናቸው።
የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ርዕይም የመደመር መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ የግንባታ ዘርፍ የማንሰራራት ጉዞ መሠረት ስንቅ ሆኗል።
ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የተለየ የቤት መግዣ ብድር መልሶ ማጠናከሪያ ኩባንያ ለማቋቋም የሚያስችለውን ታሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ይፋ አድርገዋል።
በብሔራዊ ባንክ እና በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን መካከል የተደረሰው ስምምነትም አጋርነትን በማጠናከር በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገነቡና ኢትዮጵያውያንን ክብር የጠበቁ ቤቶችን መገንባት ያስችላል።
በተለይም የ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን ግንባታ በማሳካትና በፋይናንስ ሥርዓቱ ውስጥ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማስፋት የተቀመጠውን ግብ የሚያሳካ ወሳኝ እርምጃ ነው ብለዋል።
በባንክ ዘርፉም የጥሬ ገንዘብ ፍሰት አለመመጣጠንን የሚቀርፍና በመላው ኢትዮጵያ ተደራሽ የሚሆን የቤት መግዣ ብድር ፋይናንስን የሚያስገኝ እንደሚሆን አስረድተዋል።
ሕዳሴ ግድብን እውን ያደረገው የኢትዮጵያውያን ጥንካሬና አንድነት አሁንም በዚሁ የመኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ላይ እየተደገመ ይገኛል።
ኢትዮጵያውያን በራሳቸው አቅም በዓባይ ላይ ሕዳሴን እውን እንደአደረጉ ሁሉ የዜጎቿን የመኖሪያ ቤት ጥያቄም በራሷ ጥረትና ትብብር ለመፍታት ጉዞዋን እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ለዚህም በመጪዎቹ አምስትና ስድስት ዓመታት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምረቃ ወቅት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶችን በመገንባት ለዜጎች ለማስተላለፍ ዕቅድ መያዙን አብስረዋል።
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ እያንዳንዱ የከተማና መሠረተ ልማት ግንባታ ሰው ተኮርነትንና ፍትሐዊነትን ማዕከል ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በከተማና ገጠር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው፣ ኢትዮጵያውያንን ክብር የሚመጥኑ የመኖሪያ ቤቶችና መሠረተ ልማቶች ተገንብተው ለአገልግሎት እየበቁ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የከተማና ገጠር ልማት ውጤቶችም ከሚያበረክቱት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር በሀገር ገጽታ ግንባታ ጉልህ ፋይዳ እያበረከቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ረሻድ ከማል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የተፈጠረው አስቻይ ምኅዳር ለቤት ልማት ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም በሚቀጥሉት አምስትና አስርት ዓመታት የከተሞችን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል በትኩረት እንደሚሠሩ አስረድተዋል።
የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ ታደሰ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ ምኅዳር ተፈጥሯል ብለዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ፍላጎት ምላሽ የሚሰጡ ዘመናዊ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚዎች እያስተላለፉ እንደሚገኙ አስረድተዋል።