ቀጥታ፡

አረንጓዴ ዐሻራ የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት

አረንጓዴ ዐሻራ ችግኝ መትከል ብቻ አይደለም፤ አካባቢን ለኑሮ ምቹና ማራኪ ገጽታ ማላበስ፣ የተፈጥሮን ሥነ-ምህዳር መጠበቅ፣ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ መቋቋም ጠጠር መጣል፣ ኢትዮጵያ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ የሚገዳትና ለመፍትሔውም በግንባር ቀደምትነት የምትሳተፍ መሆኗን ማሳያ ጭምር እንጂ።

አረንጓዴ ዐሻራ ለኢትዮጵያ ወንዞቿን በደለል ከመሞላት፣ አፈሯን ከመሸርሸር መታደግ፣ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና የማረጋገጥና ምድሯን አረንጓዴ የማልበስ ኢኒሼቲቭ ነው።

ከሰባት ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ኢኒሼቲቭ ሲያስጀምሩ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን በመቋቋም አይበገሬ ኢኮኖሚ መገንባት የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ አንዱ ሰበዝ እንደሆነ በመናገር ነበር።


 

ኢትዮጵያ ዛሬ ለምግብነትና ለደን ልማት አገልግሎት፣ ለአካባቢ ውበትና መናፈሻ የሚውሉ በርካታ ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል ታሪክ ሠርታለች። 

በአረንጓዴ ዐሻራ የደረቁ ሐይቆች አገግመዋል፤ በደለል የሚሞሉ ሐይቆችን መታደግ ተችሏል፤ የሚሸረሸረው ለም አፈርም ከመታጠብ ድኗል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አረንጓዴ ዐሻራ የተረጅነት ታሪክን በአዲስ ምዕራፍ በመተካት የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞ ጅማሬ መሆኑን ገልጸዋል። 

አረንጓዴ ዐሻራ ዜጎች በአካባቢያቸው የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል ለኢኮኖሚ ማንሰራራት መሠረት እየጣለ መጥቷል ብለዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ ከኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ብልፅግና ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ሀገራዊ ትልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የትውልዱ ዳግማዊ ዓድዋና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ምልክት መሆኑን ገልጸዋል። 


 

ትውልዱ እንደ ትናንቱ ዓድዋ ሁሉ የዛሬውን አረንጓዴ ዐሻራ ከአባቶቹ የወረሰው የሀገር ማስቀጠያ ስንቅ በማድረግ በታሪክ ያወሳዋል ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፤ የአረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን መሪነትና የተለየ ሚና የሚያጎላ የድል ችቦ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአረንጓዴ ዐሻራ የተመዘገበው ውጤት በአፍሪካ አህጉር የወካይነት ሚና እንዲኖራት ማስቻሉን በማንሳት፤ ዓለም አቀፋዊና አህጉራዊ ኩነቶችን ለማስተናገድ እምነት የሚጣልባት ሀገር ሆናለች ብለዋል። 

ይህም ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ በግንባር ቀደምትነት እንድትሰለፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋ፤ የአረንጓዴ ዐሻራ በአካባቢ ጥበቃ ብቻ የተገደበ ሳይሆን ለግብርና ምርትና ምርታማነት ገንቢ ሚና አለው ብለዋል። 

በኢትዮጵያ የሰብል ምርት ዕምርታዊ ለውጥ እንዲያስመዘግብ በማስቻል በስንዴ ምርት ብቻ ከተረጂነት ወደ ትርፍ አምራችነት በመሸጋገር የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እያበሰረ መሆኑን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በአቮካዶና በሌሎች የሆርቲካልቸር ምርቶች ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ እንድታገኝ አስችሏታል ብለዋል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርና ሌሎች የተቀናጁ የተፋሰስ ጥበቃ ሥራዎች በውሃ ሀብት ልማት በኩል ጉልህ ለውጥ ማስገኘታቸውን ገልጸዋል። 

የአረንጓዴ ዐሻራ የሐይቆችን የደለል ክምችት በመቀነስ ብዙ ውሃ እንዲይዙ በማድረግ የግድቦችን ዕድሜ ማራዘም አስችሏል ብለዋል። 

የደረቁ ምንጮችና ሐይቆች እንዲያገግሙ አድርጓል ያሉት ሚኒስትሩ፤ የውሃና የተፈጥሮ ሀብትን ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ማስቻሉን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም