ቀጥታ፡

የጽናት ቀን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሚያሳይ መልኩ ይከበራል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ):- ነገ ጳጉሜን 3 የጽናት ቀን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በሚያሳይ መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ።

ቀኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ያከናወኑት ተግባራት እንደሚዘከሩም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ቀኑን ማክበር የሚያስችል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች መታጠቁን ጠቁመው፣ የውስጥ እና የውጭ ፈተናዎችን በጽናት በመመከት ትልቅ ውጤት ማስመዝገቡን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለሀገርና ለህዝብ ጥቅም መረጋገጥ መሰረት መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስም የሰላም ዘብ በመሆን የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ በዚህም ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችንና ህገ-ወጥ ንግድን በመከላከልና በሌሎችም ተጠቃሽ ውጤት አስመዝግቧል ብለዋል።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርም በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጡ የሳይበር ጥቃቶችን በብቃት በመመከት የሀገር አለኝታነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎትም መረጃዎችን በመሰብሰብና በመተንተን ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ በማድረግ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትም የኢትዮጵያ ዲጂታል ጉዞ እንዲሳለጥ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ምህዳር ግንባታ ላይ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።

ነገ ጳጉሜን 3 የሚከበረው የጽናት ቀንም የጸጥታ እና ደህንነት ተቋማት ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጥበት መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸው ለላቀ ውጤት እንደሚሰራም ጨምረው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም