በብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ መስኮች የተገኙ ተጨባጭ ስኬቶች የኢትዮጵያን ማንሰራራት አመላካች ናቸው - የምጣኔ ሀብት ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
በብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ መስኮች የተገኙ ተጨባጭ ስኬቶች የኢትዮጵያን ማንሰራራት አመላካች ናቸው - የምጣኔ ሀብት ምሁራን
ቦንጋ፣ ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ)፦ በብዝሀ ዘርፍ የኢኮኖሚ መስኮች እየተመዘገቡ ያሉ ተጨባጭ ስኬቶች የኢትዮጵያ ማንሰራራትና በጽኑ የእድገት መሠረት ላይ መቆሟን የሚያመለክቱ ናቸው ሲሉ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ገለጹ።
ኢትዮጵያ ከነጠላ የኢኮኖሚ እድገት ወጥታ በብዝሀ ዘርፍ ኢኮኖሚ ባከናወነቻቸው ተግባራት በተለያዩ መስኮች ፈጣን እድገት በማስመዝገብ የማንሰራራት ጉዞ ላይ ትገኛለች።
ከግብርና መር እድገት ተላቃ ለብዘሃ የኢኮኖሚ ዘርፍ በሰጠችው ትኩረትና በመደመር መንግስት በተወሰዱ የማሻሻያ እርምጃዎች እየተመዘገቡ ያሉ ተጨባጭ ውጤቶች የሀገሪቷን ቀጣይ ብሩህ ተስፋ የሚያሳዩ ናቸው።
በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ኢትዮጵያ አሁን እየሄደችበት ያለው የማንሰራራት ጉዞ ያለመችው ብልፅግና ላይ እንደምትደርስ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህሩ ጌትነት ገዛሃኝ (ዶ/ር) እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከድህነት ታሪክ ተላቃ ወደ ቀደመ ክብሯና ገናናነቷ እንድትመለስ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።
በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቱሪዝም፣ በአረንጓዴ አሸራ፣ በሜጋ ፕሮጀክቶችና በሌሎችም የኢኮኖሚ መስኮች የተከናወኑ ተግባራት መጪውን ትውልድ ጭምር ታሳቢ ያደረጉና ሁለንተናዊ ብልጽግናን የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል።
"የኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፈ የነበሩ ማነቆዎችን በመፍታት ሥራ ያቆሙ በርካታ ፋብሪካዎች መልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በንቅናቄው የሀይል፣ የገንዘብ ብድርና የጥሬ እቃ አቅርቦት በሰፊው መሰራቱ ዘርፉ ከፍተኛ መሻሻል እንዲያሳይ ማስቻሉን ጌትነት ( ዶ/ር) ተናግረዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ከውጭ ታስገባ የነበረቸውን በርካታ ምርቶች በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ከመቻሉ በላይ የኤክስፖርት ምርቶች በመጠንና ጥራት አድገዋል ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ ለኢንዱስትሪዎችና ሌሎችም ዘርፎች በቂና አስተማማኝ የሀይል ምንጭ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በተከናወኑ ሥራዎች የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞን ያሳያሉ ሲሉ ገልጸዋል።
ሌላኛው በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲን እና የምጣኔ ሀብት መምህር ብዙአየሁ አየለ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በመደመር መንግስት በግብርናውና በኢንዱስትሪ ሴክተሮች የመጣው ተጨባጭ እድገት የሀገርን ማንሰራራት ያሳያሉ።
ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሜካናይዜሽን እርሻና ቴክኖሎጂዎችን በሰፊው ሥራ ላይ ማዋል በመቻሉ በተለይ የስንዴ ምርትን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ወደ ውጭ ለመላክ መቻሉን ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተወሰዱ እርምጃዎች ዘርፉን በከፍተኛ መጠን በማነቃቃት የማምረት አቅምን እያጎለበተ መሆኑንም ገልጸው፣ ዘርፉ ለዜጎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑንም አንስተዋል።
ቀደም ሲል ቱሪዝምን ጨምሮ ትኩረት ተነፍጎት የቆየውን የአገልግሎት ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ በመንግስት የተወሰዱ ትልልቅ እርምጃዎች እንዲሁም የተገነቡና በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሀገርን ማንሰራራት ያፋጥናሉ ብለዋል።