የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ያረጋገጡ ስኬቶች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ማንሰራራት ያረጋገጡ ስኬቶች ተመዝግበዋል
ወላይታ ሶዶ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በየዘርፉ የተመዘገቡ ስኬቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡና የሀገርን ማንሰራራት ያሳዩ መሆናቸውን ምሁራን ተናገሩ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንዳሉት በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድንና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶች አበረታች ናቸው፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህርና ተመራማሪ ሰለሞን ከበደ (ዶ/ር) እንዳሉት፣ በመደመር መንግሥት የብዝሃ ዘርፍ ኢኮኖሚ ትግበራ የመልማት አቅምን በመለየትና በቅንጅት በመስራቱ ውጤት እየተመዘገበ ነው።
ይህም የተጀመረውን ብልጽግና ጉዞ በማሳካት አስተማማኝ ኢኮኖሚን ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት በግብርና ላይ ብቻ አተኩሮ የነበረውን ኢኮኖሚ ወደ ብዝሀ ዘርፈ መቀየሩ ለዜጎች የሥራ ዕድል በማስፋትና ዘላቂ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
ለዚህም በግብርናው፣ በኃይል አቅርቦት፣ በኢንዱስትሪ ልማት፣ በቱሪዝም፣ በማዕድን ልማት፣ በአገልግሎት ዘርፎች እንደ ሀገር ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ እየተመዘገቡ ያሉ ውጤቶች የሀገርን ማንሰራራት የሚያረጋግጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው ግብርና ኮሌጅ የሰብል ልማት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ደረጀ ሻንካ (ዶ/ር) ግብርናን ለማዘመን የተከናወኑ ተግባራት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አድርጓል።
ይህም የዜጎችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ካለው ፋያዳ በተጨማሪ ለኢንዱስትሪው ግብእት በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይ በስንዴ ልማት የተመዘገበው እድገት ምርቱን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ወደውጭ መላክ መቻሉ የኢትዮጵያን ማንሰራራት በተጨባጭ ያሳየ ነው ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ዜጎች በአነስተኛ ሥፍራ ላይ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን የሚያረጋግጡበትን አቅም እየፈጠሩ መምጣታቸውንም ዶክተር ደረጀ ጠቅሰዋል።
ከግብርና ልማት ስራው በተጨማሪ በማዕድን፣ በኮንስትራክሽንና ሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ሀገሪቱ ዳግም በመነሳት አዲስ የእድገት ከፍታ ላይ እንደምትደርስ የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ ትላልቅ ሀገራዊ ግዙፍ ፕሮጀክቶችም የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ እውን እየሆነ መምጣቱንማሳያዎች ናቸው ብለዋል።