ቀጥታ፡

ጽዱ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ):- ጽዱ ኢትዮጵያን ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ በርካታ ውጤታማ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ ገለጹ።

«ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ» በተሰኘው ሀገር አቀፍ ንቅናቄ ማዕቀፍ የተዘጋጀና በአደገኛ ቆሻሻ አስተዳደር፣ በኤሌክትሮኒክስ ብክነት (e-waste) እንዲሁም በኬሚካሎች ደህንነቱ የተጠበቀ አያያዝና ማስወገድ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።


 

በመድረኩ የፌዴራልና የክልል አካባቢ ጥበቃ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የጤና ቢሮዎች ተወካዮች፣ የምርምርና የአካዳሚክ ተቋማት ተመራማሪዎች እንዲሁም በግል ዘርፍ የሚንቀሳቀሱ የቆሻሻ አስተዳደር ኦፕሬተሮች ተገኝተዋል።

የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በወቅቱ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ «ጽዱ ኢትዮጵያን» በመፍጠር በኩል በርካታ አርዓያነት ያላቸው ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡  

በዚህም የህብረተሰቡን ግንዛቤ ማሳደግ በከፍተኛ ሁኔታ መቻሉንና ለአካባቢ ጥበቃና ጽዳት ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም የሚሰራውን ስራ በማጠናከር ጽዱ ኢትዮጵያን ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘም በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያደርሱ አገልግሎት የጨረሱ ኤሌክትሮኒክስ ቁሳቁሶችና ሌሎች ቆሻሻዎችን ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

መንግስት ችግሩን ለመከላከል የሕግ ማዕቀፎችን፣ ደረጃዎችንና የሕግ ማስፈጸሚያ ሥርዓቶችን በማጠናከር በኩል የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ምክትል ዳይሬክተሯ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ችግሩን ይበልጥ ለመቅረፍ የሁሉም ርብርብ ወሳኝ መሆኑንና የመንግሥት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የምርምር ተቋማትና የሕብረተሰቡ ቅንጅታዊ አሠራር ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል።


 

በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የአካባቢ ተከባሪነትና ተፈጻሚነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ አዲሱ ጥበቡ በበኩላቸው አደገኛ ቆሻሻ ዓለም አቀፍ ትኩረት የተሰጠው ችግር መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ቆሻሻዎችን መከላከልና መቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት ዘርግታ እየሰራች ትገኛለች ብለዋል።

የፒዩር ኧርዝ የቴክኒካል ፕሮግራሚንግ ዳይሬክተር በረከት ተስፋዬ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥታ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።


 

ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር የተቀናጀ አሠራር ዘርግቶ እየሰራ መሆኑንና በቀጣይም ይህ የጋራ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

 


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም