በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች ወደ ከፍታ የሚደረገውን ጉዞ ያረጋገጡ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች ወደ ከፍታ የሚደረገውን ጉዞ ያረጋገጡ ናቸው
ነቀምቴ፣ ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ) ፡-በኦሮሚያ ክልል ባለፉት አመታት የተሰሩ የልማት ስራዎች ወደ ከፍታ የሚደረገውን ጉዞ ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጳጉሜ 02 የማንሰራራት ቀን በኦሮሚያ ክልል ደረጃ በነቀምቴ ከተማ በተለያዩ መርሃግብሮች ተከብሯል።
ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት፣ የልማት ፕሮጀክቶች ጉብኝትና የፓናል ውይይት ደግሞ ከተካሄዱት ሁነቶቹ መካከል ናቸው።
የኦሮሚያ ማዕድን ልማት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ነመራ ገበየሁ(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ በመገኘት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የቤተሰብ እና የማህበረሰቡን ብልፅግና ለማረጋገጥ በተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በተለይም የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም በማጎልበት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አንስተው፣ በዚህም የኢንዱስትሪ፣ የግብርና፣ የንግድ እና የአገልግሎት ዘርፎችን በማስተሳሰር ውጤታማ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የወለጋ ዞኖችን የልማት በር ለማድረግ እንቅስቃሴዎች እየተፋጠኑ መሆናቸውን ገልጸው፤ የተገኙት ውጤቶችም አካባቢውን ወደ ታቀደው ከፍታ ለማሻገር እንደሚረዱ ጠቁመዋል።
የማህበረሰቡን ጥያቄዎች ለሚመልሱ ሥራዎች ቅድሚያ በመስጠት፣ ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር፣ ፕሮጀክቶችን አስጀምሮ ከመጨረስ ባሻገር ተስፋን በተግባር ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
ህብረተሰቡ መንግሥት የጀመራቸውን የከፍታ ሥራዎች በማገዝ የልማት እንቅስቃሴዎች በፍጥነትና በጥራት እንዲጠናቀቁ የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
የነቀምቴ ከተማ ከንቲባ አቶ መሠረት ኃይሉ በበኩላቸው፣ "ነቀምቴ ከተማ በፈጣን የእድገት ጎዳና ላይ የምትገኝ ከተማ ናት ብለዋል።
በከተማው በተለይም በኮሪደር ልማት የተሠራው ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባሻገር፣ የነዋሪዎችን ሕይወት ያዘመነ መሆኑን ገልጸዋል።
በከተማው እስካሁን በተከናወኑ የልማት ሥራዎች የሕብረተሰቡ ተሳትፎ የጎላ እንደነበረ የገለጹት ከንቲባው፤ በቀጣይም ይህ ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አብራርተዋል።
ከተማዋን ወደ ላቀ ከፍታ ለማሸጋገር ሁሉም አካላት በመተባበር የተጀመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጠንክረን መስራት አለብን ብለዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የነቀምቴ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።