ቀጥታ፡

የኢትዮጵያና ቱርክዬን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት ይሰራል

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ እና ቱርክዬን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምክክር መድረክ በደቡብ ኮሪያ ሴኡል እየተካሄደ ይገኛል።

በምክክሩ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ አደም በጎንዮሽ የውይይት መድረክ፣ ከተርኪዬ አቻቸው፣ ከፍትህ እና ልማት ፓርቲ (አክ ፓርቲ /AK Party) ምክትል ፕሬዚዳንት ዛፌር ሲራካያ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አካሂደዋል።


 

ዘመናትን ያስቆጠረው የኢትዮ ተርኪዬ የሕዝብ ለሕዝብ እና የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት በዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተባብሮ ለመስራት እድሎችን መፍጠሩ በውይይቱ ላይ ተመላክቷል።

እነዚህን አጋጣሚዎች ይበልጥ አስፍቶ በፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነት ማስቀጠል እንዲቻል በብልፅግና ፓርቲ እና በአክ ፓርቲ መካከል በጋራ ለመስራት በ2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተፈረመው የሁለትዮሽ ስምምነት አጋዥ እንደሆነ በውይይቱ ላይ ተነስቷል።

በዋናነትም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተለያዩ መስኮች አጠናክሮ በመቀጠል፣ የወጣቶች እና የሴቶች ክንፍን በጋራ የልምድ ልውውጥ መስኮች ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ እንዲሁም በአቅም ግንባታ መድረኮች የአመራሮችን አቅም በቀጣይነት እየገነቡ ለመሄድ የታቀዱ ስራዎች ወደ ተግባር ሊቀየሩ እንደሚገባ ተነስቷል።


 

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ የፓርቲ ለፓርቲ ግንኙነትን ማጠናከር ለሀገራት ግንኙነት መጠናከር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ ብልፅግና ፓርቲ በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የተርኪዬ ፕሬዝዳንት ረጀብ ጣይብ ኤርዶጋን በተደጋጋሚ መገናኘት የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረሱን ጠቅሰዋል።

እስከአሁን የተደረሱ የሁለቱ ሀገራት ስምምነቶችን ከግብ ለማድረስ ቀጣይነት ያለው ጥረት እንደሚደረግ አንስተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ እና በአክ ፓርቲ መካከል እ.አ.አ በ2025 የተፈረመው የመግባቢያ ስምምነት በአግባቡ ተፈፃሚነት እንዲኖረውም የጋራ መድረኮችን ከማካሄድ ባለፈ ዝርዝር አፈፃፀሙ ላይ ጠንካራ ክትትል የሚያደርግ አካል እንደሚመደብ ቃል ገብተዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው የኮፕ32 ጉባዔም በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀም የኮፕ31 አስተናጋጅ የሆነችው ተርኪዬ ልምዷን በማካፈል ረገድ እያደረገች ያለውን ጥረት አድንቀው፣ ለሁለቱም ዝግጅቶች ስኬት የጋራ ትጋታቸው አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በጋራ አረጋግጠዋል።

ቱርኪዬ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን የከፈተችበት እ.አ.አ በ2026 100ኛ ዓመቱን አስቆጥሯል።

በሁለቱ ገዥ ፓርቲዎች መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ለቀጣዩ ክፍለ ዘመን የጠበቀ ወዳጅነት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።

አያይዘውም ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስና ወደ ከፍተኛ ሀገራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ለመቀየር ብልፅግና ፓርቲ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም