ቀጥታ፡

ትውልዱ የህብረተሰቡን ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና እሴት ጠብቆ የማስተላለፍ  ኃላፊነት አለበት

አመያ፣ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፡-ትውልዱ  የህብረተሰቡን ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋና እሴት  ጠብቆ የማስተላለፍ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን  የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኮንታ ዘመን መለወጫ  "ህንግጫ" በዓል በአመያ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።


 

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የኮንታ ዘመን መለወጫ ህንግጫ በአል በትውልድ ቅብብሎሽ የተገነባ ውድ ቅርስ ነው።

በመሆም የበአሉን ታሪካዊ ዳራ ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

በክልሉ ባለፉት አመታት  በሁሉም ዘርፎች ብልጽግናን ማረጋገጥ የሚያስችሉ እምርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ እነዚህ ድሎች ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ላይ እንደሆነች ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

በክልሉ ባለፉት አመታት  ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉም አመላክተዋል፡፡

የተያዘውን  የማንሰራራት ጉዞ ለማፋጠን በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የትብብርና የጋራ ጥረቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ።


 

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉ በበኩላቸው ህንግጫ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲከበር የመጣ  የኮንታ የማንነትና አንድነት መገለጫ ነው ብለዋል።

በአሉ የሕዝቡን አንድነት፣ ፍቅር፣ አብሮነትና ተስፋ ከማጠናከር ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።

በበአሉ ላይ የፌደራል፣ የክልልና በየደረጃው ያሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢው ማህበረሰብና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም